አገልግሎቱ ፓስፖርት የማደስና አዲስ የመስጠት ተግባሩን በመቀሌ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
አገልግሎቱ ፓስፖርት የማደስና አዲስ የመስጠት ተግባሩን በመቀሌ ጀመረ

መቀሌ ፤ ነሐሴ 13/2016(ኢዜአ)፡- የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት የመቀሌ ቅርንጫፍ አዲስ የፓስፖርት ማደስና መስጠት አገልግሎቱን ዛሬ በመቀሌ ከተማ መጀመሩ ተገለፀ።
በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የመቀሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ምትኩ ታከለ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ አዲስ ፓስፖርት ለሚያወጡና ነባር ፓስፖርት ለሚያድሱ ደንበኞች በኦን ላይን የታገዘ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ማንኛውም ፖስፖርት ፈላጊ በየትኛውም የክልሉ አካባቢ ሆኖ አዲስ የፓስፖርት አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችለውን መስፈርት በማሟላት በኦን ላይን ማመልከት እንደሚችል አስረድተዋል።
በዚህም ደንበኞች አዲስ የፓስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ሲመጡ የአካባቢውን አስተዳደር የድጋፍ ደብዳቤና የልደት የምስክር ወረቀት /ሰርተፊኬት/ በማቅረብ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉም ተናግረዋል።
የጽሕፈት ቤቱ ሰራተኞችም ተገልጋዮችን በቅንነት ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውንም አስተባባሪው አስታውቀዋል።
ከተገልጋዮቹ መካከል አቶ ገብረሕይወት ግደይና ወጣት ገብረእግዚአብሄር ግርማይ በከተማው የነባር ፓስፖርት እድሳትና የአዲስ ፓስፖርት መስጠት አገልግሎት በመጀመሩ ከአላስፈላጊ ወጪና እንግልት ታድጎናል ብለዋል።
በየአካባቢው የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ቢሮዎችም ቀልጣፋ አግልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባ የተናገረው ደግሞ ወጣት ማዕረግ ግርማይ ነው።
በተለይ የድጋፍ ደብዳቤ እና የወሳኝ ኩነት አገልግሎትን የሚሰጡ የመስተዳደር ፅህፈት ቤቶች ፈጣን አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባም አመልክቷል።