በአማራ ክልል ለመጠባበቂያ እህል ክምችት የሚውል የሰብል ልማት ተጀምሯል -ግብርና ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ለመጠባበቂያ እህል ክምችት የሚውል የሰብል ልማት ተጀምሯል -ግብርና ቢሮ

በባህርዳር ነሐሴ 15/2016 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ከተረጅነት ለመላቀቅና እርዳታን በራስ አቅም ለመሸፈን በ36ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመጠባበቂያ እህል ክምችት የሚውል ሰብል ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከተረጅነት ለመላቀቅና እርዳታን በራስ አቅም ለመሸፈን ለመጠባበቂያ እህል ክምችት የሚውሉ የተለያዩ ሰብሎችን የማልማት ስራ ተጀምሯል።
በክልሉ በ2016/17 ምርት ዘመን ልማቱን በ36 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለማካሄድ ታቅዶ እስካሁን ከ27 ሺህ 700 ሄክታር የሚበልጥ መሬት በመለየት ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
በመኽር ወቅቱ እስካሁን 4 ሺህ 695 ሄክታር መሬት ታርሶ በበቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ማሽላ፣ ገብስና ሩዝ ሰብሎች በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።
ቀሪውን መሬት ለማልማት ጥረቱ የቀጠለ መሆኑን አመልክተዋል።
ለምርት ማሳደጊያ የሚውል 1 ሺህ 914 ኩንታል ማዳበሪያና 1 ሺህ 154 ኩንታል ምርጥ ዘር ቀርቦ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ተናግረዋል።
የሰብል ልማቱ በመንግስት የልማት ድርጅቶችና ሌሎች አካላት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
"በራስ አቅም የመጠባበቂያ እህል በማምረት ዕርዳታን ሳንጠብቅ ለተረጂዎች በማከፋፈል ክልሉን ከተረጅነት ነፃ ለማድረግ የተያዘው ግብ እንዲሳካ የሚመለከታቸው ተቋማት የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርጉ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል ።
የክልሉ መሬት ቢሮ የገጠር መሬት ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ በላይ በበኩላቸው፤ በዕቅድ ከተያዘው መሬት አብዛኛው ተለይቶ ወደ ልማት እንዲገባ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደተቻለም አስረድተዋል።
በክልሉ ከሁሉም ዞኖች መካከል ከወል መሬት፣ ከተቋማት፣ ከመሬት ባንክና በባለሃብቶች ተይዞ ሳይለማ ከቆየ መሬት በመለየት ለሰብል ልማቱ እንዲውል መደረጉን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።