የክትመት ምጣኔ ለማሳለጥ ኢ-መደበኛ አሰፋፈርን መልክ ማስያዝ ይገባል 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 4/2017(ኢዜአ)፦ የክትመት ምጣኔ ለማሳለጥ ከመሰረተ-ልማት ግንባታና ከአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ባሻገር ኢ-መደበኛ አሰፋፈርን መልክ ማስያዝ እንደሚገባ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም "ዘላቂ የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063" በሚል መሪ ኃሳብ ባለፈው ነሐሴ መጨረሻ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። 

ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው በዚህ ፎረም ከ47 በላይ የአፍሪካ አገራት፣ ከ30 በላይ የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች፣ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። 

በፎረሙም የክትመት ምጣኔዋ በፍጥነት እያደገ ከተሜነቱ ገና የሆነባት አፍሪካ ያሏት መልካም ዕድሎችን ለችግሮቿ የሚያስፈልጉ የመፍትሔ ኃሳቦች ላይ ውይይት ተደርጓል። 

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሄለን ደበበ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማት ያሳካችውን ልምድ ያካፈለችበት ከሌሎችም የቀሰመችበት ነበር። 

በተለይም የዜጎችን ተጠቃሚነት ባረጋገጠና አካታችነት ባለው መልኩ የተከናወኑ የከተማ ማደስ ሥራ እንዲሁም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ማዕቀፍ የተሰሩ ሥራዎች ኢትዮጵያ በፎረሙ በተሞክሮነት መቅረቧን ጠቅሰዋል።

በተለይም የኮሪደር ልማቱ በአዲስ አበባ ከተማ አጭር ጊዜ ውስጥ ያመጣው ለውጥ ትልቅ ልምድ የተቀሰመበት እንደነበርም አንስተዋል። 

በአፍሪካ ከተሜነት ገና ቢሆንም የክትመት ምጣኔው በፍጥነት እያደገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በፍጥነት እየመጣ ያለውን ክትመት የሚመጥን የመሰረተ ልማት ግንባታ ያስፈልጋል ብለዋል። 

ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ያለው የክትመት ምጣኔ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር እስከ 2050 የከተማ ነዋሪዎችን በእጥፍ ያሳድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። 

ከተሞችን ለዜጎች ምቹና ተስማሚ ለማድረግና የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታ መፋጠን እንዳለበት ጠቁመዋል።

ለክትመት እንቅፋት የሆነውን ኢ-መደበኛ አሰፋፈር መልክ ማስያዝ እንደሚገባ ጠቅሰው ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያም በትኩረት እየሰራች መሆኗን ተናግረዋል።  

ከተሞች የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን መቀነስ በሚያስችል መልኩ በቴክኖሎጂ ታግዘው መገንባት ይኖርባቸዋል ብለዋል። 

በአፍሪካ ያለው የተፈጥሮ ኃብትና የሰው ኃይል አቅም ለከተሜነት መስፋፋት ገንቢ አበርክቶ እንዳለው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ ፈተና ይዞ እንደሚመጣም ተናግረዋል።

በመሆኑም በቀጣይ የሚኖረውን የከተማ ነዋሪ ብዛት ታሳቢ በማድረግ ፈጠራን ያማከለ አሰራር መዘርጋት ይገባል ብለዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም