መርሃ ግብሩ ጥሪት አፍርተን ከድህነት እንድንላቀቅ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል - ተጠቃሚዎች

ጎንደር፤ ህዳር 28/2017(ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተመቻቸው የድጋፍ መርሃ ግብር ሀብትና ጥሪት አፍርተው ከድህነት እንዲላቀቁ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች ተናገሩ። 

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት ጽህፈት ቤት በመርሃ ግብሩ ታቅፈው ሀብትና ጥሪት ያፈሩ አንድ ሺህ 500 ነዋሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።

በከተማው የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች መካከል አቶ ሰለሞን አየነው በሰጡት አስተያየት፤ ሴፍቲኔት ጠንክሮ በመስራት መለወጥ እንደሚቻል የተማርኩበትና በተግባር አልፌ ራሴን የቻልኩበት ነው ብለዋል።


 

ባለፋት ሶስት ዓመታት በመርሃ ግብሩ ታቅፈው ከዕለት ምግብ በተጨማሪ በተደረገላቸው የብድር ድጋፍ አንድ የወተት ላምና፣በጎችና ዶሮዎችን በመግዛት ወደ ስራ መግባታቸውን አውስተዋል።

አሁን ላይ ተጨማሪ ጥሪት ለመያዝ እንዳበቃቸው ጠቁመው፤ መርሃ ግብሩ ለሌሎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ተደራሽ እንዲሆን አመልክተዋል። 

ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ረኸመት አድኖ፤ አረብ ሀገር ሄደው ከፍተኛ እንግልት ደርሶባቸው ባዶ እጃቸውን መመለሳቸውን አስታውሰዋል።

በከተማ ሴፍቲኔት መርሃ ግብሩ ታቅፈው ባገኙት ብድር የባልትና ውጤቶች ሱቅ በመክፈት ከ400ሺህ ብር በላይ ካፒታል ማፍራት መቻላቸውን አስረድተዋል።

በጥልፍና በልብስ ስፌት ሙያ ባገኘሁት ስልጠና በመታገዝ አሁን ላይ ከቤተሰብ ጠባቂነት ለመላቀቅ በቅቻለሁ ያለችው ደግሞ ሌላዋ ተሳታፊ ናድያ ጡሃ ናት። 


 

አሁን  የልብስ ስፌት መኪና ባለቤት ከመሆኔም በላይ ከ200ሺህ ብር በላይ መንቀሳቀሻ ካፒታል  ማፍራት በመቻሌ ለወደፊት ትልቅ ደረጃ ለመድረስ እንዳልም አነሳስቶኛል ብላለች።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሃዲያ መሃመድ እንደገለጹት፤ በከተማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ 20ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች በመርሃ ግብሩ ታቅፈው ይገኛሉ።


 

ባለፉት ሶስት ዓመታት በመርሃ ግብሩ ታቅፈው በየወሩ ከሚከፈላቸው ገንዘብ ባሻገር በተደረገላቸው ድጋፍ ሀብትና ጥሪት ያፈሩ አንድ ሺህ 500 ነዋሪዎች ዛሬ ለምረቃ መብቃታቸውን አረጋግጠዋል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው፤ መርሃ ግብሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ህይወት በመቀየር ረገድ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሱለይማን እሸቱ እንዳሉት፤ በክልሉ 122ሺህ ቤተሰቦችን ያቀፉ 30ሺህ አባወራዎች በልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር ታቅፈው ይገኛሉ። 


 

በክልሉ በ18 ከተሞች በሚካሄደው መርሐ ግብር በዚህ ዓመት ሀብትና ጥሪት አፍርተው ለሚመረቁ 10ሺህ  700 አባወራዎች የመቋቋሚያ ገንዘብ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር አባላት በተገኙበት ለመርሀ ግብሩ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት የእውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም