ሰላማዊ ሰልፉ ሕዝባችን ምን ያክል ሰላም እንደሚሻ ያሳየበት ነው-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 9/2017(ኢዜአ)፦ዛሬ በአማራ ክልል የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ሕዝባችን ምን ያክል ሰላም እንደሚሻ ያሳየበት ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፥ በአማራ ክልል የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም፥ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፍ መካሄዱን ተናግረዋል።ሰላማዊ ሰልፉ ግጭት በቃን፣የምንፈልገው ሰላምና ልማት ነው የሚል መልዕክት የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕዝቡ የደገፈው ሰላምን ነው ያሉት አቶ አረጋ ከበደ፥ ሰላማዊ ሰልፉ ሕዝባችን ምን ያክል ሰላም እንደሚሻ ያሰያበት ነው ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ሰልፎች እንዳይካሄዱ ለማስፈራራት እና ለማሸበር የተደረገው ጥረትም አልተሳካም ነው ያሉት። ሕዝቡ ግን ዛቻ እና ማስፈራሪያዎችን በመተው ሰላምን እንደሚፈልግ በነቂስ ወጥቶ አሳይቷል ብለዋል።

ሰልፉ ጥያቄ አለኝ የሚል ኃይል ሁሉ ችግሮችን በውይይት ነው መፍታት የሚገባው የሚለውን የሚያሳስብ መኾኑንም አመላክተዋል።

ሕዝብ ከጎናችን ነው እያለ መንግሥትን በኃይል እናስወግዳለን የሚለውን ኃይል ያጋለጠ መኾኑን ተናግረዋል።

ሰልፉ እንደ መንግሥት ልዩ ትርጉም አለው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ መንግሥት ለሰላም ያደረገውን ጥረት በአደባባይ ወጥቶ የደገፈበት ነው ብለዋል።

ዛሬ ሕዝቡ መንግሥትን ብቻ አይደለም የደገፈው፣ የደገፈው ሰላምን ነው ብለዋል። ሰላም ሲኾን ለመንግሥት ትልቅ ዓቅም መኾኑን ነው የተናገሩት።

ዛሬ የተደረገው የሰላም ሰልፍ በቀጣይ ለሚደረገው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ጉልበት የሚፈጥር ነው ብለዋል።በሕዝባችን ትልቅ ኩራት ተሰምቶኛል፣ ምስጋናም እናቀርባለን ነው ያሉት። ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ላደረጉ የጸጥታ ኃይሎች ምስጋና አቅርበዋል።

የዛሬው ሰልፍ ወደፊት ለሚደረገው የሕግ ማስከበር እና የሰላም ሥራ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።

መንግሥት ሰላማዊ አማራጮችን ቀዳሚ የችግር መፍቻ አድርጎ እንደሚጠቀምም አስታውቀዋል። አውዳሚ ተግባርን አንመርጥም፣ የምንመርጠው ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣውን ሰላማዊ አማራጮችን ነው ብለዋል።

ችግሩ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሰላም አማራጮችን መፈለጋቸውን እና ማስቀመጣቸውን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ የሰላም አማራጭ ለይስሙላ የምናደርገው ሳይኾን አምነንበት እና አዋጭ መኾኑን ተረድተን የምናደርገው ነው ብለዋል።

የዛሬው ሰላማዊ ሰልፍ ሕዝብ ሰላማዊ አማራጮችን ብቻ እንደሚፈልግ ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።በሰላማዊ አማራጮች የማይጠቀሙት ላይ የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት እንደሚገባ የተረጋገጠበት መኾኑን ነው የተናገሩት።

የክልሉ ሕዝብ በአንድነት ወጥቶ ባሳየው የሰላም ፍላጎት ኮርተናል፣ ምስጋናም ይገባዋል ብለዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም