የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የመረጃና የደኅንነት ተቋማት የሚያደርጉትን ሁሉን-ዓቀፍ ትብብር አጠናክረው ለመቀጠል የሚያግዝ ውይይት አካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የመረጃና የደኅንነት ተቋማት የሚያደርጉትን ሁሉን-ዓቀፍ ትብብር አጠናክረው ለመቀጠል የሚያግዝ ውይይት አካሄዱ

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የተቋሙ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሎችና ከፍተኛ አመራሮች በደቡብ ሱዳን ኢንተርናል ሴኪዩሪቲ ቢሮ ዳይሬክተር ጀነራል ሌተናል ጀነራል አኬች ቶንግ አሉ ከተመራ የልዑክ ቡድን ጋር በሁሉን-ዓቀፍ የትብበር ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸውን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለኢዜአ የላከው መረጃ አመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ጠንካራ የሆነ ታሪካዊ፣ ባሕላዊና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ያላቸው ሀገራት እንደሆኑ በምክክር መድረኩ መነሳቱን ያመለከተው መረጃው፤ የጋራ ዕጣ-ፈንታቸውንና ሕልውናቸውን የሚወስኑ ዘርፈ-ብዙ ትብብሮች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ትስስር ለማረጋገጥ የሚገነባው የመንገድ መሠረት ልማት ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሳድግ መሆኑ በውይይቱ ወቅት መነሳቱን ያመለከተው የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መረጃ፤ በዚህ ሂደት ከጸጥታና ከደኅንነት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በመረጃ ልውውጥና በጋራ በሚደረጉ ስምሪቶች መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች መምከራቸውን አስታውቋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ እንደገለጸው፤ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በድንበር አካባቢ የሚታዩ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ፣ የገንዘብና የሰዎች ዝውውርን ለመግታት እንዲሁም የሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል የሚያደርጓቸውን የትብብር ሥራዎች አጠናክረው በመቀጠል ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማስፈን ይሠራሉ፡፡
ከዚህ ቀደም የደቡብ ሱዳን የመረጃና ደኅንነት አመራሮችና ባለሙያዎች በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስልጠና መውሰዳቸውን የጠቆመው መረጃው፤ በሰው ኃይል ዐቅም ግንባታ ረገድ የሚደረገው ትብብርም ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን ገልጿል፡፡
በደቡብ ሱዳን ኢንተርናል ሴኪዩሪቲ ቢሮ ዳይሬክተር ጀነራል የተመሩት የልዑካን ቡድኑ አባላት በአዲስ አበባ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማቶችን እና ሌሎችንም ፕሮጀክቶች የጎበኙ ሲሆን፤ በከተማው በሚታዩት ፈጣን እድገቶችና ለውጦች መደነቃቸውን እንደገለጹ መረጃው ጠቁሟል፡፡
ሌተናል ጀነራል አኬች ቶንግ አሉ ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ሱዳን ኢንተርናል ሴኪዩሪቲ ቢሮ በዳይሬክተር ጀነራልነት በመሾም ሀገራቸውን እያገለገሉ መሆናቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ የላከው መረጃ የጠቆመ ሲሆን፤ በመረጃ፣ በደኅንነትና በጸጥታ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረጉ ትብብሮች ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያድጉ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ መግለጻቸውን አመልክቷል፡፡