የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎቶች በፍትህ ስርዓቱ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎቶች በፍትህ ስርዓቱ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16/2017(ኢዜአ)፦ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎቶች በፍትህ ስርዓቱ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በማጠናከር የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ በትኩረት እንዲሰሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም የቦሌ ምድብ ችሎቶች የለውጥ ስራዎች ላይ የመስክ ምልከታ አድርጓል።
በንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ ችሎት የሚገኙ የባንክና ኢንሹራንስ፣ የኮንስትራክሽንና ንግድ ችሎቶች እና በቦሌ ምድብ ችሎት አገልግሎት አሰጣጥን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በሁለቱም ምድብ ችሎቶች በቴክኖሎጂ በመታገዝ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተግባራዊ የተደረጉ የለውጥ ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት ከተገልጋዮችና ከሰራተኞች ጋር ውይይት በማድረግ በፍርድ ቤቶች ላይ የተደረጉ የለውጥ ስራዎችና በተጨባጭ የመጡ ለውጦች እንዲሁም ክፍተቶች ላይ ተወያይተዋል።
አዲስ የተከፈተውን የንግድና ኢንቨስትመንት ችሎትን ጨምሮ ተደራሽነትን ለማስፋት፣ ለመዝገቦች ፈጣን እልባት ከመስጠት፣ አገልግሎትን ከማዘመን አንጻር ለውጦች መምጣታቸውን ተገልጋዮች አንስተዋል።
ዳኞች በበኩላቸው በችሎቱ የሚመጡ ጉዳዮችን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በነጻነት ስራቸውን እንደሚያከናውኑ በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል።
የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ በፍትህ ዘርፍ የዳኝነት አሰጣጥ ላይ እየተደረጉ ያሉ የለውጥ ስራዎች ያመጡት ለውጥና ቀጣይ ትኩረት ማግኘት ያለባቸው ጉዳዮችን ማመላከት የመስክ ምልከታው አላማ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የለውጥ ስራዎችን እየተገበረባቸው ከሚገኙ ዘርፎች አንዱ የፍትህ ስርዓቱ መሆኑን ገልጸው የመስክ ምልከታ ባደረጉባቸው ምድብ ችሎቶች አበረታች ለውጦችን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ ካርታን ለመተግበር የንግድና ኢንቨስትመንት ችሎትን ጨምሮ የችሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ከተከናወኑ ጠንካራ ስራዎች መካከል ጠቅሰዋል።
በጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ መሰረት ለጉዳዮች እልባት ለመስጠት፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት፣ አሰራርን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የተጀመሩ ስራዎችንም እንዲሁ።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የበለጠ ማሳደግ፣ የተገልጋይ ዕርካታን የሚጨምሩ አገልግሎት መስጠት፣ የህዝብ አመኔታን መጨመር ቀጣይ በትኩረት መሰራት ያለባቸው እንደሆኑም አሳስበዋል።
የምድብ ችሎቶቹ ተጠሪ ዳኞች የተሰጡ ግብረ መልሶችን በመውሰድ፣ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠልና ለመዝገቦች ፈጣን እልባት በመስጠት የተገልጋይ እርካታን ለመጨመር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።