የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስብራቶች የሚጠግኑ ገዥና አሰባሳቢ ትርክቶችን መፍጠር ያስቻሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል-ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 17/2017(ኢዜአ)፦በለውጡ አመታት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስብራቶች የሚጠግኑ ገዥና አሰባሳቢ ትርክቶችን መፍጠር ያስቻሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር)፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የፖለቲካ ባህል ለመገንባት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የለውጥ ሙከራዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

የ2010 ዓ.ም የለውጥ መነሻም የፖለቲካ ስብራቶች መነሻ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በተለይም ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት አለመገንባት፣ የነጻና ገለልተኛ ተቋማት ግንባታ ችግር፣ አሰባሳቢ የሆነ ገዥ ትርክት አለመፍጠር፣ ደካማ የፖለቲካ ባህልና ሌሎችንም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ማናቸውንም ችግሮች በውይይት ከመፍታት ይልቅ የግጭትና ጦርነት አዙሪቶች እስካሁንም ለዘለቁ ችግሮች ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል።

በእነዚህና ሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች ዘርፈ ብዙ ሃብቶች ያሏትን ሀገር በድህነት ዘመናትን እንድትቀጥል ያደረጋት መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የለውጡ መንግስት እነዚህን ስር የሰደዱ የፖለቲካ ስብራቶች ለመጠገን የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎችን በመውሰድ የሚታዩና የሚጨበጡ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

ለአብነትም በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሀገር እንዲመራ የተመረጠው የብልፅግና ፓርቲ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን የመንግስት ስልጣን ይዘው እንዲሰሩና ህዝብን እንዲያገለግሉ ማድረጉን ተናግረዋል

በዚህም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የፖለቲካ ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ መስራት አለብን የሚለውን እሳቤ ይዘው እንዲሰሩ ማድረጉን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ ሂደት ተቀራርቦ የመስራትና በሃሳብ የበላይነት የመነጋገር ባህልን ያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ ማንኛውንም ሀሳብ ወደ ጠረጴዛ እንዲያመጡ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን አንስተው መንግስትም በሆደ ሰፊነት ወደ ውይይት እንዲመጡ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በዋናነት በታኝ የነበረውን ዋልታ ረገጥና የነጠላ ትርክት በመተው አሰባሳቢና ገዥ ትርክት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያን ከነበረችበት ችግር የሚያወጡ አሰራሮችን በመዘርጋት በለውጡ አመታት ነጻና እና ገለልተኛ ተቋማትን የመገንባት ስራዎች በስኬታማነት ተከናውነዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም