ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላም እና ደኀንነት መጠበቅ ያላትን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 17 /2017(ኢዜአ ):-ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላም እና ደኀንነት መጠበቅ ያላትን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለነባር ዲፕሎማቶች እና ለወጣት በጎ ፈቃደኛ ካዴቶች ስልጠና እየተሰጠ ነው።


 

በስልጠናው ዙሪያም አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በምሥራቅ አፍሪካ ሰላም እና ደኀንነት በተመለከተ የኢትዮጵያ ሚናን ገለፃ አድርገዋል።

አምባሳደሩ፥ ኢትዮጵያ ቀጣናው አስተማማኝ ሰላም እና ደኀንነት እንዲጠበቅ እንዲሁም የተረጋጋ እንዲሆን ከሌሎች አገራት ጋር ጉርብትናን በማጠናከር በትብብር እንደምትሰራ ገልጸዋል።

ተለዋዋጭ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በመርህ ላይ በመመስረት በኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ግንኙነት መስኮች እንዲጠናከሩ በጋራ መስራት እንደሚገባ አንስገንዝበዋል።

የአገርን ብሔራዊ ጥቅም በተሟላ ሁኔታ ለማስከበር እና የሕዝብን አደራ ለመወጣት በመጭው የካቲት ወር አጋማሽ በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ዲፕሎማቶች እና ወጣት በጎ ፈቃደኛ ካዴቶች በአገር ፍቅር ስሜት ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም