በክልሉ በህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት በተሰማሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት በተሰማሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው

ታህሳስ 20/2017(ኢዜአ)፡-በህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት በተሰማሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ገሾ፤ በክልሉ በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠር በየዕለቱ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ በጋራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በተደረገው የቁጥጥርና ክትትል ሥራም በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት አምስት ወራት ከ226 ሺህ ሊትር በላይ ህገ ወጥ ነዳጅ እና የነዳጅ ውጤቶች ተይዘው ወደ 13 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ለመንግስት ገቢ መደረጉን ተናግረዋል።
በተደረገው ቁጥጥርና ክትትል በህገ-ወጥ የነዳጅ ንግድ ላይ የተሰማሩ 44 ሰዎች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱንና እስከ ሰባት ዓመት እስራት የተቀጡ መኖራቸውንም አስረድተዋል።
ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ እድገት ነዳጅ መሠረታዊ ግብዓት መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ሀላፊው፤ በተለይም የትራንሰፖርት አገልግሎት፣ የእርሻ ማሽነሪዎችና የሌሎች ነዳጅ ተጠቃሚዎች ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የነዳጅ አቅርቦት እንዲኖር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በሀገሪቷ በቂ የነዳጅ አቅርቦት ቢኖርም በህገ ወጥ መንገድ ላልተፈቀደለት ዓላማ በመዋሉ አልፎ አልፎ እጥረት አንዲከሰት ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ቢሮው ይህን ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በኤክትሮኒክስ ግብይት ብቻ አንዲፈፀም የተደረገ ሲሆን ቅንጅታዊ የክትትልና ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በክልሉ የነዳጅ ንግድ ላይ መሰማራት የሚቻለው በመመሪያው መሠረትና ተያያዥ ሠነድ ይዞ በመገኘት ብቻ እንደሆነም አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል።
ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይቱ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ወደ ጠረፍ ድንበርም እየተዘዋወረ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ሀላፊው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ህብረተሰቡ በእኔነት ስሜት ከመንግሥት ጎን በመቆም ለፍትህ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።