በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመስኖ ልማት የተሰጠው ትኩረት የአርብቶ አደሮችን ህይወት እያሻሻለ ነው-ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 25/2017(ኢዜአ)፦በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመስኖ ልማት የተሰጠው ትኩረት የአርብቶ አደሮችን ህይወት በእጅጉ እያሻሻለ መሆኑን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን የጎዴ መስኖ መሰረተ ልማት ፕሮጀክትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።


 

የጎዴ መስኖ መሰረተ ልማት ፕሮጀክት 27 ሺህ 600 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው ሲሆን በአካባቢው የሚኖሩ ከ53 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያድርግም ተገልጿል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ፤ መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ በተለይም ለመስኖ ልማት በሰጠው ትኩረት የአርብቶ አደሮች ህይወት በእጅጉ እየተሻሻለ መሆኑን ተናግረዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎችም በቂ የግብርና ጥሬ እቃ እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፤በገጠር የሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ወጣቶች በዘርፉ የስራ ዕድል ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ብለዋል።

የሶማሌ ክልል በበርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች የታደለ ቢሆንም ከልማት እርቆ መቆየቱን አስታውሰው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ማልማት ባለመቻሉ ለድርቅና ጎርፍ ተጋላጭ እንደነበርም ጠቅሰው፥አሁን ላይ ሁለንተናዊ ልማት እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።

በየአካባቢው ያሉ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም፣ በየወረዳው አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ልማት ሥራዎችን በማከናወን በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ብለዋል።

የፌደራል መንግስት በቆላማ አካባቢዎች ያሉ እምቅ አቅሞችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ትኩረት መስጠቱንም ነው የገለጹት።

በዚህም የጎዴ መስኖ መሰረተ ልማት ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት መግባቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የቆላማ አካባቢ የመስኖ ልማት እና የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች በምግብ ራስን ለመቻል እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጎዴ መስኖ መሰረተ ልማት ፕሮጀክትም ለክልሉ ልማት ከሚያበረክተው ሚና ባሻገር ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም