ለኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ለውጥ ብቁ የሂሳብ ባለሙያዎችን ማፍራት አስፈላጊ ነው - የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 25/2017(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ለውጥ ብቁ የሂሳብ ባለሙያዎች የሚያፈራ ኢንስቲትዩት ማቋቋም ተገቢ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩትን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።


 

ረቂቅ አዋጁን ካቀረበው የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ሃላፊዎች ጋር ትርጓሜ፣ ማስተካከያና ማብራሪያ በሚያስፈልጋቸው ድንጋጌዎች ላይ ሰፊ ጥያቄዎችን በማንሳት ውይይት ተደርጓል።

በረቂቅ አዋጁ እንዲቋቋም የቀረበው ኢንስቲትዩት የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎችን ለማፍራት ስርዓተ ትምህርት የመቅረጽ፣ የመመዘንና የሙያ ማጎልበቻ ስልጠናዎችን የመስጠት ሃላፊነት ያለው ነው።

ኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብቷን ለአለም አቀፍ ተቋማት ክፍት በማድረግ ዘላቂ ምጣኔ ሃብት ለመገንባት እያከናወነች ላለው ተግባር ብቁ የሂሳብ ሙያተኞችን ማፍራት ወሳኝ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል።

ለዚህም የአለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት እና የኦዲት ብቃት ደረጃዎችን ለማሟላት በቂና ብቁ የሂሳብ ሙያተኞችን ለማፍራት ኢንስቲትዩቱን ማቋቋም የሚኖረው ፋይዳ ላይ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

በተመሳሳይ የሚቋቋመው ኢንስቲትዩት ከዘርፉ የሙያ ማህበራትና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተለየ የሚኖረው አስተዋጽኦ ላይ ማብራሪያ ጠይቋል።

በሌላ በኩል ከምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የህግ ጉዳዮች ጥናት ዳሬክቶሬት ባለሙያዎች ረቂቅ አዋጁ ከሌሎች አዋጅና መመሪያዎች ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ መታየት ያለባቸው ጉዳዮችን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ተጠባባቂ ዋና ዳሬክተር ፈቃዱ አጎናፍር የረቂቅ አዋጁ ዋና ትኩረት ብቃት ያላቸው ሙያተኞችን ማፍራት የሚያስችል ኢንስቲትዩት ማቋቋም መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ የሚገኙ የሙያ ማህበራት ረዥም እድሜ ያስቆጠሩ ቢሆንም ከሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ለውጥ ጋር የሚጣጣም ሙያተኛ ማፍራት ባለመቻላቸው ኢንስቲትዩት ማቋቋም አስፈልጓል ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ የሂሳብ ባለሙያዎች አለም አቀፍ ስልጠናዎችን ለማግኘት የሚያወጡትን ወጪ የሚያስቀር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተዘዋውረው መስራት የሚችሉበትን እውቅና የሚሰጥ መሆኑንም ጨምረዋል።

ማንኛውም ግለሰብ ስልጠና መውሰድ እንደሚችል ካለው ተገቢነት አንጻር ፣ አካታችነትና ሌሎች በትኩረት መታየት ያለባቸው የአዋጁ ድንጋጌዎች ላይ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቶበታል።

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ ኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎችን የሚያፈራ ኢንስቲትዩት ባለመኖሩ በዘርፉ ያለውን ክፍተት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለምትፈጽማቸው አለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነቶች፣ ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ለተደረገው የባንክ ዘርፍና ሌሎች የምጣኔ ሃብት ለውጦች አለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው የሂሳብ ባለሙያዎችን ማፍራት ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ተግባራዊ እየተደረገ ላለው ምጣኔ ሃብት ለውጥ የተሟላና ግልጽ የፋይናንስ ሪፖርት የሚያቀርብ ባለሙያ የሚያፈራ ተቋም ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት፣ የታክስ አስተዳደርን ለማዘመንና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል ብለዋል።

በአዋጁ ከትርጓሜ፣ ከአገላለጽ፣ ማስተካከያ ከሚያስፈልጋቸውና ሌሎች ድንጋጌዎች ላይ የተነሱ አስተያየቶችን በመውሰድ በትኩረት መታየት እንዳለበት በማሳሰብ በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግበት አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም