የአየር ትንበያ አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽና ዘመናዊ ለማድረግ የሚያግዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ትንበያ አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽና ዘመናዊ ለማድረግ የሚያግዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ

ሮቤ፤ የካቲት 2/2017(ኢዜአ)፡- የአየር ትንበያ አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽና ዘመናዊ ለማድረግ የሚያግዙ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ጣቢያዎችን ማስፋትና ማዘመን ላይ ትኩረት ያደረገ ዐውደ ጥናት በባሌ ሮቤ ተካሂዷል።
በኢንስቲትዩቱ የዳታና ክላይማቶሎጂ ዳይሬክተር አቶ መለሰ ለማ በወቅቱ እንዳመለከቱት፤ ኢንስቲትዩቱ የአየር ትንበያ አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽና ዘመናዊ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።
በአሁኑ ወቅትም ከዓለም አቀፍ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎትና ሌሎች ተቋማት በተገኘ የበጀት ድጋፍ አገልግሎቱን የማስፋትና የማዘመን ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም 16 አዳዲስ የምድርና የአየር ላይ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ጣቢያዎችን ለመስራት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች በመመቻቸት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የደቡብ ኦሮሚያ ሚቲዎሎጂ አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሙላቱ ወርቅነህ በበኩላቸው ፤ ማዕከሉ የአየር ትንበያ መረጃዎችን ለተጠቃሚዎች በየጊዜው እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
የሚቲዎሮዎሎጂ አገልግሎቶችን ይበልጥ ማስፋትና ማዘመን ከዕውነታ ጋር የተቀራረባ የአየር ትንበያ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
አቶ ሙላቱ እንዳሉ፤ ማዕከሉ በደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በቀጣይ የበልግ ወቅት 35 በመቶ ከመደበኛ በላይ፣ 40 በመቶ መደበኛና 25 በመቶ ከመደበኛ በታች እንደሚሆን ተተንብየዋል።
ባለድርሻ አካላትም በተለይ ከመደበኛ በታች እንደሚያገኙ የተተነበዩ አካባቢዎች አርሶ አደሮች ማሳቸውን ፈጥነው በሚደርሱ የሰብል ዓይነቶች እንዲያለሙ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ መክሯል።
በመድረኩ ላይ ከተሳተፉ ባለድርሻ አካላት መካከል የባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ዳዲ፤ ከአገልግሎቱ በየወቅቱ የሚገኘው የአየር ትንበያ መረጃ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀምና ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ደግሞ ለመቀነስ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የደቡብ ኦሮሚያ ሜትሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ከሚሸፍናቸው አካባቢዎች መካከል ሁለቱ ባሌዎች፣ ቦረና ፣ጉጂ ፣ ከፊል አርሲና ምዕራብ አርሲ ዞኖች እንደሚገኙበት ተመልክቷል።