ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ መሻሻል አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ መሻሻል አለባቸው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2017(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ መሻሻል እንዳለባቸው በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ።
46ኛው የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የስራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሔደ ይገኛል።
በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በዚህ ወቅት፤ አፍሪካውያን የተፈጥሮ ሀብታቸውን በአግባቡ መጠቀም አልቻሉም ብለዋል።
አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የምታሳድረው ተፅዕኖ ጥቂት ቢሆንም የጉዳቱ ገፈት ቀማሽ መሆኗን ገልጸዋል።
በመሆኑም የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ ሪፎርም መደረግ አለባቸው ብለዋል።
የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ስርዓት በመሰረታዊነት መቀየር እንዳለበትም ገልጸዋል።
አፍሪካውያን አህጉራዊ ሀብታቸውን እሴት ጨምረው መጠቀም እንዲችሉ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በአህጉሪቱ ጥሬ ምርትን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ በምርቶች ላይ እሴትን ጨምሮ የመላክ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
አፍሪካውያን ለደረሰባቸው ግፍና በደል ተገቢ የፍትሕ ካሳ ሊያገኙ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ይህ ችግር የዓለም የንግድ ስርዓትን በማዛባት የአፍሪካውያንን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በእጅጉ የጎዳ መሆኑን ተናግረዋል።
አፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላት አሉታዊ ተፅዕኖ ውስን ቢሆንም የጉዳቱ ሰለባ ከመሆን አልዳነችም ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ አፍሪካን የአህጉራዊ ጥቅል ምርቷን አምስት በመቶ እንደሚያሳጣት በመጥቀስ፣ በዓለም ዙሪያ ለኢንቨስትመንት ከሚመደበው ሀብት የአፍሪካ ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ይሄ የአፍሪካን ጥቅም የሚጎዳ ኢፍትሃዊነት በቃህ ሊባል ይገባል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት መሰረታዊ ሪፎርም ሊደረግባቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።