የአፍሪካውያን የዛሬ ስራ ለነገ ተስፋቸው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካውያን የዛሬ ስራ ለነገ ተስፋቸው

በዓለም በትልቅነቷ በሁለተኝነት የምትጠቀሰው አፍሪካ የህዝብ ቁጥሯ በ2024 (እ.ኤ.አ) አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
አህጉሪቷ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች፣ የሰጡትን የሚያበቅል ለም አፈር ያላት፣ ከራሷ አልፋ ለሌሎች የምትተርፍ መሆኗም በብዙዎች የተመሰከረለት ነው።
ይሁንና አህጉሪቷ ለበርካታ ዓመታት በጦርነት፣ በበሽታ፣ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ስትጠቃ ኖራለች።
ከተመሰረተ 50 ዓመታትን የተሻገረው የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት "እ.ኤ.አ በ2063 መሆን የምንፈልገው" ብለው የተለያዩ እቅዶችን ነድፈው ወደ ተግባር ገብተዋል።
''እኛ አፍሪካውያን በ2063 መሆን የምንፈልገው'' በሚል ባሰፈሩት አጀንዳ በርካታ የአህጉሪቷ የልማትና የብልጽግና ትልሞች ተቀምጠዋል።
በዚህም ሁሉን አቀፍ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት የተረጋገጠባት፣ በልማትና በኢኮኖሚ የተዋሃደች፣ ሰላምና ደህንነቷ የተጠበቀና በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ የጎለበተ አህጉር መፍጠር ይገኙበታል።
በኢኮኖሚ የፈረጠመች፣ የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠችና ለዜጎቿ ምቹና አስተማማኝ አህጉር የማድረግ እቅዱን ለማሳካት የተለያዩ ጥረቶች ተጀምረዋል።
የአገራቷ መሪዎችም እነዚህን የልማት እቅዶች ከየአገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለገቢራዊነቱ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል።
አፍሪካ በ50 ዓመታት ለማሳካት የያዘችው አጀንዳ ሁሉን አቀፍ የልማት እቅድ፣ ከዓለም ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታና በአፈጻጸም ቁርጠኝነት ክፍተት እስካሁን የሚፈለገውን ያህል ውጤት ያለመመዝገቡም ይገለጻል።
መሪዎቹ ይህን እቅዳቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር የነበራቸው ቁርጠኝነት ማነስ፣ የውጭ ተጽእኖ ማየል ዕቅዶቹ እንዳይሳኩ ምክንያት ሆነዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጽዕኖን የምታስተናግደው አፍሪካ አሁንም ቢሆን ተደጋጋሚ ድርቅና ጎርፍን እንዲሁም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዜጎቿን እየፈተኑ ይገኛሉ።
የምርትና ምርታማነት እጥረት፣ የሰለጠነ የሰው ሃይልና ቴክኖሎጂ አቅም ውስንነት፣ የሌሎች አገራት ጣልቃ ገብነትና ሌሎች ችግሮችን በመፍታት አጀንዳዋን ለማሳካት ብዙ ይቀራታል።
አፍሪካ በ50 ዓመታት ውስጥ ለመሳካት ያቀደችውን በተግባር ለማጠናቀቅ 38 ዓመታት ይቀሯታል።
በዚህ ረገድ የተወሰኑ አገራት የተሻለ ኢኮኖሚ በማስመዝገብ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና፣ መሰረተ ልማትና ቴክኖሎጂን በማሟላት የተሻለ ዕድገት ማስመዝገባቸው ይነገራል።
በአህጉሪቷ በተመሰረቱ የተለያዩ ጥምረቶች አገራት እርስ በእርስ በመሰረተ ልማትና በሃይል በማስተሳሰር ረገድ መልካም የሚባሉ ጅምሮች ታይተዋል።
ይሁንና የዓለምን ተለዋዋጭ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች በአግባቡ በመረዳት የዜጎችን ህይወት በተጨባጭ መቀየር፣ ሰላማዊ፣ በኢኮኖሚ የዳበረች፣ በዓለም መድረክ እኩል ድምጽ ያላት አህጉር የመፍጠር እቅዱን እውን ለማድረግ በርካታ ቀሪ ስራዎች መኖራቸው የአደባባይ ሀቅ ነው።
እያንዳንዱ አፍሪካዊ ዜጋ አጀንዳ 2063ን በአግባቡ ተገንዝቦ ለትግበራው የድርሻውን መወጣት እንዲችልም በቂ የግንዛቤ ስራ ሊሰራ ይገባል።
የአፍሪካ መሪዎች በአጀንዳ 2063 የተያዙ ግቦች በትክክል እንዲተገበሩ ዜጎቻቸውን አስተባብረው በቁርጠኝነት መስራት ግድ ይላቸዋል።
የአጀንዳ 2063 እውን መሆን ዋነኛ ተጠቃሚ የሚያደርገው የአህጉሪቷን ዜጎች እንደመሆኑ እቅዱን ለማሳካት አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው።
የአፍሪካ አገራት የጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ለመምከርና የአህጉሪቷን መጻዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግ በአንድ ጥላ በሚያሰባስባቸውና በዓመት ሁለት ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ላይ ይገናኛሉ።