አዲስ አበባ በአሕመድ ሴኩ ቱሬ አንደበት - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ በአሕመድ ሴኩ ቱሬ አንደበት

(62 ዓመታት ወደኋላ)
________________
አሕመድ ሴኩ ቱሬ ከቀደምት የፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኞች አንዱ ነበር። በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር በነበረቸው የምዕራብ አፍሪካዊነቷ ሀገረ-ጊኒ የነጻነት ታጋይና ፖለቲከኛ ናቸው። ድሕረ ነጻነት የሀገሪቷ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆነዋል። በፈረንጆቹ አቀጣጥርግንቦት 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ ከታደሙና አስደማሚ ንግግር ካሰሙ መሪዎች መካከል አንዱ ሴኩ ቱሬ ነበሩ። ለዛሬ ከፕሬዝዳንት አሕመድ ሴኩ ቱሬ አዲስ አበባን እና ኢትዮጵያን በወቅቱ የገለጹበትን መንገድ እነሆ ብለናል።
“…. አዲስ አበባ የታሪክ ክስተት መውጠኛ ስፍራ ናት። በአፍሪካ አወንታዊ የለውጥ ሽግግር ታሪክ መቁጠሪያ ነጥብ ሆናለች። ይህ ቅጽበት የአፍሪካ የተሟላ አርነት ማብሰሪያ ነው፤ የአፍሪካ ሰው ከነምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊ፣ ወታደራዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ውቅሩ ነጻ የሚወጣበት። ይህ ስፍራ አፍሪካዊያን መንግስታትን ውጤታማ የሚያደርግ የፈጠራ ክዋኔዎች የመለኮሻ ዘመንም ነው። ለምን ቢሉ አፍሪካዊያን ወደ አንድ በመመጣት ህዝባቸውን ከሰቆቃ እንዲያገግም፣ የጋራ ስልጣኔ እንዲያንሰራራ፣ ሰብዓዊ እሴቶችና ባህላቸው ፈጣን እመርታ እንዲያመጣ ግብ የሰነቁበት ነውና።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ነው። ኢትዮጵያዊያን ለአፍሪካ ነጻ መውጣት በጀግንነት ተዋግተዋል። የሕዝብ ነጻነት እንዲጠበቅ ብሎም ሰዎች ያለማንም የውጭ አካል ጣልቃገብነት መብታቸው ተከብሮ መዳረሻቸውን በራሳቸው ይተልሙ ዘንድ መንገድ የጠረጉ እና የራሳቸውን ጉዳይ በተሟላ ሉዓላዊነት እንዲፈጽሙ በተግባር ያሳዩ ህዝቦች ናቸው።
ዛሬ በኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ የአፍሪካ ጉባዔ እየተካሄደ ነው። ይህም ኢትዮጵያ ምንጊዜም በአፍሪካ ታሪክ ገጾች ውስጥ ደማቅ አሻራ አንብራለች። መላው የአህጉሪቷ ህዝብ የመለወጥ መሻቱን በቅጡ እንዲገነዘብ የተካሄደ ሁነት ነው።
በ1885ቱ(በአውሮፓዊያን አቆጣጠር) የበርሊን ጉባዔ በኢኮኖሚ የጠገቡ ስርዓት አልበኛ የአውሮፓ መንግስታት ስልጣኔያቸውን ለማስፋፋት ሲሉ ያላቸውን ሀይል ተመክተው አፍሪካን እንደ ኬክ ቆራርሰው ሊቀራመቱ ተሰባስበው ነበር። ዛሬ ግንቦት 1963(በአውሮፓዊያን) ግን ምርጥና ሐቀኛ የአፍሪካ ልጆች ስለራሳቸው እና ስለእናት ምድር አፍሪካ ታምነው በንጹህ ማንነት የጋራ መዳረሻ መንገድ ለመቀየስ አዲስ አበባ ተሰባስበው እየመከሩ ነው።
የአፍሪካ ትንሳኤዋ ዛሬ ነው። አፍሪካ በአንድ ነጠላ መንግስት ህጋዊ መልክ ትይዝ ዘንድ ልዩ መተዳደሪያ ሰነድ(ቻርተር) ማለትም አፍሪካዊያንን በወንድማማችነት፣ በማይናወጥ አጋርነት፣ በሰዎች መብትና ጥቅም፣ በሰላምና ነጻነት እንዲሁም በፍትህ መርሆች ውህደት የሚፈጥሩበት አጋጣሚ ነው።
የአዲስ አበባ ጉባዔ የዛሬን አፍሪካ ችግሮች ምላሽ በመስጠት ላይ ብቻ የተወሰነም አይሆንም። አፍሪካ የዓለም አካል መሆኗን ልብ ይሏል። በዓለም ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሰው ልጅ ሕይወት፣ ሰላም፣ ደህንንትና ዕድገት መንስኤ የሆኑ የጋራ ተግዳሮቶች ሁሉ አፍሪካን ይገዷታል…”።