የአድዋን መንፈስ እንልበስ- ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሌይ

ወርሃ የካቲት የጥቁሮች ወር ነው። ካሪቢያን ጥቁሮች በጥቁሮች የትግል ታሪክ ጉልህ አሻራ ያላቸው መሰረተ አፍሪካ ህዝቦች ናቸው። ካሪቢያን ዜጎች ኢትዮጵያን አብዝተው ይወዳሉ። ለመላው ጥቁር ሕዝቦች አንድነትና ትግል ንቀናቄ አድዋን እንደ እርሾና እሴት ያወሳሉ። በቅርብ በ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የታደሙት የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሌይ በሕብረቱ ጉባዔ ላይ ያደረጉት ንግግር በርካቶችን ያስደመመና ያስደነቀ ነበር።

ከመልዕክታቸው ውስጥ ተከታዮቹን ሃሳቦች መዘናል፦

👉 አድዋ በ24 ሰዓታት ውስጥ የአውሮፓዊያንን የራስ መተማመን ትምክህት ያሽመደመደ፤ የአፍሪካዊያንና ትውልድ አፍሪካዊያንን ልጆች መንፈስ ያጎመራ፣ መልካምነት ድል ያደረገበት፣ ብርሃን በጨለማ ላይ የነገሰበት ሁነት ነው።

👉 ዛሬ እናንተ ፊት የቆምኩት ይህን መንፈስ ታጥቄ ነው። አድዋ የፓን አፍሪካኒዝም እርሾ ነበር።

👉 የአድዋ ድል ለነጻነትና ትግል እንድንነሳሳ ባቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነጻነት ድል እንድንቀዳጅ ምዕራፍ የከፈተ ድል ነው። አድዋ የአንድነት ውጤት ነው።

👉 እናንተ ፊት የቆምኩት የፓን አፍሪካዊነት ፈር ቀዳጆችን ሕልም ሰንቄ  ነው።

👉 እኛ የካረቢያን ትውልዶች ከአፍሪካ ወንድምና እህቶቻችን ጋር ሕብረታችንን ማጠናከር እንሻለን።

👉 ትናንት በእኛ መከፋፈል ራሳቸውን ለበላይነት ያነገሱ ሃይሎችን እያሰብን አንድነታችንን አጠናክረን ነገን እንገንባ ወይም እንደ ትናንቱ ተነጣጥለን እንጥፋ የሚለው ምርጫ የኛ ፋንታ ነው። 

👉 ስለዚህ የአድዋን  መንፈስ ተላብሰን ከፊታችን የሚጠብቀንን መልከ ብዙ ፈተና በአንድነት እንጋፈጥ።

👉 ከአፍሪካ ውጭ የጥቁሮች ምድር ከሆነችው ባርባዶስ ተነስቼ ኢትዮጵያ የተገኘሁት ለአፍሪካና ካረቢያን ህዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት ጥሪ ነው።

👉 ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥለሴ በዓለም ላይ አንደኛና ሁለተኛ መደብ ዜጋ መኖር የለበትም እንዳሉት ዛሬም በየትውልዱ በዓለም ላይ ኢ-ፍትሃዊነትና አግላይነት ስርዓት ይወገድ ዘንድ መታገል አለብን። ለዚህ ደግሞ የአድዋ ድልና የፓን አፍካዊነት መንፈስን እንልበስ።

👉 የጋራ መዳረሻችንን ለመቀየስ ከወሬ ይልቅ ተግባር ላይ አተኩረን በትጋት እንስራ። የትናንት ቁስልን እያከክን ሳይሆን ብሩህ ነገን ለመገንባት በጋራ እንቁም።

👉 ከፊታችን የተደቀነ አደገኛ ፈተና እንዳለ ተገንዝበን ፈተናውን በአንድነት ለመጋፈጥ ሞራላዊ ግዴታችንን እንወጣ።

👉 የአድዋን መንፈስ እንልበስ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም