የካቲት እና ኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
የካቲት እና ኢትዮጵያ

በአየለ ያረጋል
በየክፍላተ-ዓለሙ ዓመታት በወራት ሲመነዘሩ የራሳቸው መልክና መገለጫ ይኖራቸዋል። እንደየንፍቀ ክበቡ ወቅቶች የራሳቸው ጸባይ፣ ክዋኔ፣ ትውስታና ትዕምርት ይቸራቸዋል።
ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ባለ13 ወር ጸጋ ናት። ከጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመርም ሰባት ዓመት ከስምንት ወራት ልዩነት አላት። በባሕር ሃሳብ ምሁራን የኢትዮጵያን ወቅቶች መጸው(መኸር)፣ ሐጋይ(በጋ)፣ ፀደይ(በልግ) እና ክረምት በሚል አራት ወቅቶችና አውራኅ ይከፍሉታል።
ሁሉም አውራኅ፣ እያንዳንዱ ወራት በራሳቸው ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቀለማትን ይጎናጸፋሉ። የወራቱ ቅላሜና ሕብርነት ልዩ መልክዓ-ኢትዮጵያን ይፈጥራል። ከዘመን መባቻው መስከረም እስከ ማዕዶተ-ዘመኗ ጳጉሜን ወራቱ በሰማይና በምድሩ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ውቅራቸው ግላዊ ገጽታ ይነበብባቸዋል።
የኢትዮጵያ ወራት ስያሜ ከመልክና ግብራቸው ይመነጫል። ከሁሉም ወራት ግን ከታሪካዊ ሁነቶች አንጻር የካቲት ልዩ ገጽታ አለው። አሁን ወቅቱ በጋ ወይም ሐጋይ ነው። ወርኅ የካቲትንም የሐጋይ አውራኅ ደማቁ ገጽ ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ውስጥ ወርኅ የካቲትን ያክል በየታሪክ ህዳጉ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ የወሰነ ወቅት ያለ አይመስልም።
የካቲት የበጋ ወርኅ አልፎ የበልግ ጊዜ መግቢያ ነውና የቋንቋ ሊቃውንቱ 'የካቲት'ን ስያሜ 'የመከር ጫፍ መካተቻ፤ የበልግ መባቻ " ይሉታል። የመኸር ምርት የሚከተትበት ነው። በኢትዮጵያ ዘመን ስሌትም መንፈቅ ዓመት ወይም ስድስተኛው ወር ነው።
ወርኅ የካቲት በመካከለኛው ዘመን ዝነኛውን ንጉስ አፄ ሠርፀድንግልን፣ የአድያምሰገድ ኢያሱን ልጅ ዳግማዊ አፄ ዳዊት(አድባር ሰገድን)፣ “የዘመናዊት ኢትዮጵያ ጠንሳሽ ናቸው” የሚባሉትን አፄ ቴዎድሮስንና ንግስት ዘውዲቱን አንግሷል።
በሌላ በኩል ኢማም አሕመድ ኢብራሂምን(ግራኝ አህመድ)፣ አፄ ሚናስን፣ እቴጌ ጣይቱን፣ እቴጌ መነንን፣ ንጉስ ወልደጊዮርጊስን፣ ራስ ደስታ ዳምጠውን፣ ራስ አሉላ እንግዳን እና ሌሎች የዓድዋ ብሔራዊ የጦር ጀግኖችን አሳርፏል።
ከኪነ-ጥበብ መስክ ደግሞ ወርኅ የካቲትን ያህል የሞት ዶፍ የወረደበት ወቅት እንደሌለ ብዙዎቹ ይስማማሉ። ለአብነትም ሞገደኛው ብዕረኛ አቤ ጉበኛ እረፍት የካቲት 2፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር የካቲት 12፣ ጸጋዬ ገብረመድህን የካቲት 18፣ ማሞ ውድነህ የካቲት 23፣ እንዲሁም ተወዳጁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ እንደወጣ የቀረው የካቲት 24 ነበር። የካቲት በርካታ የምንኮራባቸው ሰዎች የተወለዱበትና በሞት ያጣንበትም ወር ነው።
የካቲት ታላቅ የሰማዕትነት ወር ነው፤ በ1929 ዓ.ም 30 ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በጅምላ በአካፋና በዶማ በግፍ የተጨፈጨፉት በወርኅ የካቲት ነው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የጣሊያን ወራሪን በማሳፈር ለጥቁር ሕዝቦች ቀንዲል የሆነውን የዓድዋ ድል የተቀዳጀችው በየካቲት መገባደጃ ወቅት ነበር። መልከ-ብዙው ዓድዋ ድል፤ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ተከውኗል።
በዚያች ተዓምረኛ ዕለት በዓድዋ ተራሮች መንደር መድፎች አጓርተዋል፤ መትረየሶች አሽካክተዋል፤ እሳት ወርዷል፤ ጥይት ዘንቧል፤ ጎራዴ ተመዟል፤ ጦር ተሰብቋል። በጥቅሉ የክቡር ሰብዓ ዘሮች ደም ተገብሯል።
የዓድዋ ድል ህያውነት፣ እንቆቅልሽነት፣ አድማስ ዘለል ታሪክነት፣ የዓለም ነፀብራቅነት፣ አፍሪቃዊነት፣ ኢትዮጵያዊነት ተዘርዝሮ አያልቅም፤ በዓድዋ ጦርነት የተመዘገቡ የይቅርታ፣ የፍቅርና የርህራሄ እሴቶች ከጥቁር ሕዝቦች ድልነት አሻግረው ለእያንዳንዱ ሰው ድል አድርገውታል።
ከየካቲት ድሎች ዓድዋ ይድመቅ እንጂ ቅድመ-ዓድዋም ሆነ ድኅረ-ዓድዋ ጦርነት ደማቅ ድሎች ተመዝግበዋል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ በወርኅ የካቲት የግብጽን ወረራ በጉራ፣ የሶማሊያ ጦርነትን በካራማራ፣ ድል ተቀዳጅታለች።
የካቲት 12 ጭፍጨፋ እና የካቲት 23 የዓድዋ ድልን ጨምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የማንነት፣ የሀዘን ሁነቶችና ተፃራሪ ታሪኮችን አስተናግዷል ይኸው ወርሃ የካቲት።
የ1928ቱ የጣሊያን ወረራ በሽሬ፣ በተንቤን እና በአምባራዶም የጦር ሜዳዎች የተከለከለ መርዝ በኢትዮጵያዊያን ላይ ተርከፍክፎ እንዲቃጠሉ መደረጉም የታሪክ ድርሳናት እማኝ ናቸው።
ወርኅ የካቲት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ታላላቅ አብዮቶች፣ ታላላቅ ድሎች ተከውነውበታል። ለኢትዮጵያ ሕልውና እንደ ክብር የደም ግብር የቀረበበት፣ በየጋራና ሸንተረሩ የትውልድ መስዕዋትነት የተከፈለበት ጊዜ ነው። የካቲት የድልና የዕድል፤ የደምና ገድል ወር ነው። አሳዛኝም፤ አስደሳችም!
የካቲትና የኢትዮጵያ ታሪክ ግንኙነት ድል የተገኘበት፣ መጥፎ ጠባሳዎችንም ያተምንበት ወቅት በመሆኑ ወርኅ የካቲትን በግጥምጥሞሽ የተሞላ፤ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር ተነጥሎ የሚታይ አይደለም።
የካቲት ወር 2010 ዓ.ም በኢህአዴግ ላይ የነበሩ አመጾች የተባባሱበትና ፖለቲከኞች ከእሥር የተፈቱበት ነው። የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኃላፊነት ለመልቀቅ ለፓርቲው መልቀቂያ ደብዳቤ ያቀረቡበት ነው።
ከኢትዮጵያ አልፈው እንደ ዓድዋ ያሉ ለጥቁር ሕዝቦች ትግል አብነት የሆኑ ታሪኮች የተፈጸሙበት፣ አብዮት የተካሄደበትና የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የተወሰነባቸው ክስተቶችን ያስተናገደ ወር እንደሆነ ያነሳሉ።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የማንነት፣ የሀዘን ሁነቶችን ማስተናገዱን አስተናግዷል። የወርሃ የካቲት ሁነቶች ተጻራሪ ታሪኮች እንደሆኑ የካቲት 12 እና የካቲት 23ን ለአብነት ይጠቀሳሉ።
በርግጥ ወርኅ የካቲት ከኢትዮጵያ አልፎ በአጠቃላይ የመብትና ነፃነት ትግሎች የተስተናገዱበት ሲሆን በአገረ- አሜሪካ ጥቁሮች ለእኩልነትና ነፃነት የታገሉበት ወቅት በመሆኑ የታሪካቸው አካል በማድረግ ያከብሩታል።
ለመሆኑ ወርኅ የካቲት ከኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ጋር የመጣባቱ ምስጢር ምን ይሆን?
ለጉዳዩ አመክንዮ የሰጡ የታሪክ ምሁራን ወርሃ የካቲት ገበሬው የሚያርፍበት፣ ወንዞች ደርቀው ሰው የሚገናኝበት በመሆኑ እንዲሁም የጾም ወቅት መሆኑ የውጭ ጠላቶች አስልተው እንደሚመጡ ጠቅሰው፤ ለአብነትም በሰንበትና በፆም ወቅት የተደረገውን የአድዋ ጦርነት ያነሳሉ።
ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ገበሬ የሆነባት ኢትዮጵያ ካሏት 13 ወራት መካከል ወርኃ የካቲት ለገበሬው ጥጋብ፣ ለመንግስታት ደግሞ የግብር መሰብሰቢያ ወር መሆኑን በማውሳት።
ወርኃ የካቲት ምርት ተሰብስቦ ጎተራ የሚገባበት፣ ሰርግ የሚሰረግበት፣ ሽፍታ የሚበረታበት ወቅት ነው። በ'ግብር ገብር! አልገብርም!' በሚል ግብግብ የገበሬ አመጽ የታየበት ወር መሆኑ ይወሳል።
በሌላ በኩል ወቅቱ ተማሪዎች ከአንደኛው መንፈቅ ዓመት ወደ ሁለተኛው የሚሸጋገሩበት ነው። በዚህም ተማሪዎችም ለንቅናቄ ይነሳሳሉ። በ1960ዎቹ የተደረገውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመሬት ለአራሹ፣ የዴሞክራሲ፣ የኃይማኖትና የብሔር ጥያቄዎችን ያነሱበትና አብዮት የቀሰቀሱበት እንደነበር የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ።
የካቲት በርካታ የምንኮራባቸው ሰዎች የተወለዱበትና ያጣንበትም ወር መሆኑን ለምን ብለን ባንጠይቅም፤ ግጥምጥሙ ግን አጃይብ ያሰኛል።
ኢትዮጵያ በየካቲት ወር ባሳለፈቻቸው ታሪኮች ልትማር፣ ትውልዱም ታሪኩን ሊያውቅ ይገባል።