በትግራይ ክልል በበጋ መስኖ ቀይ ሽንኩርት ያለሙ አርሶ አደሮች ተጠቃሚነታቸው መጨመሩን ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል በበጋ መስኖ ቀይ ሽንኩርት ያለሙ አርሶ አደሮች ተጠቃሚነታቸው መጨመሩን ገለፁ

መቀሌ፤ መጋቢት 5/2017 (ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን በበጋ መስኖ ቀይ ሽንኩርትና የቀይ ሽንኩርት ዘርን ያለሙ አርሶ አደሮች የተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ገለፁ።
በክልሉ በአሁኑ ወቅት የአካባቢውን የአየር ንብረት መሰረት ያደረጉ የፍራፍሬና የሽንኩርት የልማት ስራዎች በስፔሻላይዜሽን የመከወን መልካም ጅምሮች እየታዩ መሆናቸውም ተገልጿል።
በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን በራማ ዓዲ አርባዕተ የሓድሽ ዓዲ ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ሐጎስ ንጉስ ለኢዜአ እንደገለፀው የሚኖርበት አካባቢ የአየር ንብረቱና አፈሩ ለቀይ ሽንኩርት ልማት ተሰማሚ መሆኑን በመገንዘብ አንድ ጥማድ መሬት ላይ ካለማው ቀይ ሽንኩርት 12 ሺህ ብር ገቢ አግኝቷል።
ይህን ካፒታል እንደ መነሻ በመጠቀምም አሁን በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ያለማው ቀይ ሽንኩርት በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ ስለሚገኝ ለልማቱ ያወጣውን ወጪ ሸፍኖ ከ300 ሺህ ብር በላይ ትርፍ እንደሚጠብቅ ተናግሯል።
ከሌላ ጓደኛው ጋር ሽርክና በመፍጠር በሁለተኛው ዙር ከአራት ሄክታር መሬት በላይ ቀይ ሽንኩርት ለማልማት መሬት እያለሰለሱ መሆናቸውን ወጣት ሀጎስ አስረድተዋል።
ከወራጅ ወንዝ በጄኔሬተር ውሃ በመሳብ ከሁለት ኪሎ ሜትር በላይ በመውሰድ ከስድስት ሄክታር መሬት በላይ ቀይ ሽንኩርት በማልማት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር መኮንን ገብረመድህን ናቸው።
አርሶ አደር ተስፉ ተወልደ በበኩላቸው የቀይ ሽንኩርት ዘርን በማባዛት ላይ ብቻ ትኩረት /ስፔሻላይዝድ/ በማድረግ ሁለት ጥማድ መሬት በማልማት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የቀይ ሽንኩርት ዘር የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው በማወቃቸው ሁለት ጥማድ መሬት የቀይ ሽንኩርት ዘርን በማባዛት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው ከዚሁ ምርት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር እንደሚጠብቁም ገልፀዋል።
በደቡባዊ ምስራቅ ዞን የእንደርታ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ወጣት አርሶ አደር ፀጋዘአብ በርሀ በበኩሉ በገበያ ላይ ያለውን አዋጭነት በመገንዘብ የቀይ ሽንኩርት ዘርን ወደ ማባዛት እንደተሸጋገረ ገልጿል።
አንድ ጥማድ መሬት በመከራየት አልምቶ ሁለት ኩንታል የቀይ ሽንኩርት ዘር በመሰብሰብ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ትርፍ ማግኘቱን ተናግሯል።
ከአሁን ቀደም ከውጭ ይመጣ የነበረውን የቀይ ሽንኩርት ዘር በአካባቢያቸው መተካት መጀመራቸውን ጠቁሞ በዘርፉ ስፔሻላይዝድ በማድረግ በቀጣይ አራት ሄክታር መሬት ላይ ለማልማት ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጿል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበራ ከደነው እንደገለፁት በክልሉ በአሁኑ ወቅት የአካባቢውን የአየር ንብረት መሰረት በማድረግ በተለየ ሁኔታ ፍራፍሬና ሽንኩርትን የማልማት መልካም ጅምሮች እየታዩ ናቸው።
አሁን የተጀመሩት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በምርጥ ዘር አቅርቦትና በሌሎች የቴክኒክ ድጋፎች እየተደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት 93 ሺህ ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ 210 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።