በክልሉ ተማሪዎች ስለ ግብርና ታክስ በቂ እውቀት ይዘው እንዲያድጉ ግንዛቤ እየጎለበተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ተማሪዎች ስለ ግብርና ታክስ በቂ እውቀት ይዘው እንዲያድጉ ግንዛቤ እየጎለበተ ነው

ቦንጋ፤መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፦የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ተማሪዎች ስለ ግብርና ታክስ በቂ እውቀት ይዘው እንዲያድጉ የታክስና ጉምሩክ ክበባት ተቋቋመው ግንዛቤ እያጎለበቱ መሆኑ ተገለጸ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አቀፍ የታክስና ጉምሩክ ክበብ ተማሪዎች የጥያቄና መልስ የውድድር መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሄደ።
ከመሠረቱ የተገነባ ትውልድ ሀገርን ይገነባል" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ውድድሩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ የገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ነው።
በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አልማው ዘውዴ እንዳሉት፣ ተማሪዎች ስለ ግብርና ታክስ በቂ እውቀት ኑሯቸው ታማኝ ግብር ከፋይ እንዲሆኑ የታክስና ጉሙሩክ ክበባት ሚና የላቀ ነው።
ለዚህም በክልሉ ባሉ ትምህርት ቤቶች ክበባትን በማደራጀት ተማሪዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ተሳተፎ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ተማሪዎች ላይ መስራት ነገ ሀገርን የሚወድና ግብሩን በታማኝነት የሚከፍል ትውልድ ማፍራት ነው' ያሉት ሀላፊው ግብርንና ታክስን በታማኝነት የሚከፍል ትውልድን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል'' ብለዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሕይወት አሰግድ በበኩላቸው በክልሉ የተጀመሩ ልማቶችና የዜጎች ፍላጎት ለመመለስ ገቢን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ክልሉ ሲመሰረት ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥታ ያልሆነ ታክስ እና ታክስ ያልሆነ ገቢ ሲሰበሰብ ከነበረበት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ዘንድሮ ወደ 10 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ገቢውን አሟጦ ለመሰብሰብ የተለያዩ አደረጃጀቶች በመጠቀተም ስልጠናዎች እና ምክክሮች እየተደረጉ መሆናቸውን ያነሱት ወይዘሮ ሕይወት፣ ከዚህም ዋናው የትምህርት ትቤቶች የታክስ እና ጉምሩክ ክበባት መሆናቸውን ገልፀዋል።
በየትምህርት ቤቶች የተጀመሩ የታክስ እና ጉምሩክ ክበባት ትውልዱ የታክስ እና ጉምሩክ አስተዳደር ምንነትን እና ህጎች ላይ መሰረታዊ እውቀት እንዲኖራቸው እና ህገ-ወጥነት እና ኮንትሮባንድን የሚፀየፍ ዜጋ እንዲሆኑ ማስቻል ነው ብለዋል።
የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር ጅማ ቅርንጫፍ ስራ የታክስ አስተዳደር ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ነጋሶ አብዲሳ፣ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ የሀገር ጉዳይ በመሆኑ ለማሳካትም ግንዛቤ ማስፋት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ግብር ከፋዩ፣ ማህበረሰቡና ትውልዱ ስለግብር ግንዛቤ እንዲሰፋ በትምህርት ቤት ደረጃም የተለያዩ ክበባትን በማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው የገቢ አሰባሰብ አቅም እንዲጨምር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በመድረኩ ላይ የክልል አመራሮች፣ ርዕሰመምህራን፣ተማሪዎችና ሌሎች ባለድሻዎች ተገኝተዋል።