የአፍሪካዋ ግዙፍ መዲና -አዲስ አበባ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካዋ ግዙፍ መዲና -አዲስ አበባ

አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ የገበያ ባለሙያ እና የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር ክሪስ ቦራቲን በዴይሊ ኤክስፕረስ ጋዜጣ ቋሚ አምደኛ ነው። ክሪስ ቦራቲን በእንግሊዙ ዕለታዊ ጋዜጣ ዴይሊ ኤክስፕረስ ላይ ስለ መዲናዋ በከተበው ጽሁፍ ላይ። ጋዜጠኛው በጋዜጣው ላይ በዓለም ላይ ሊጎበኙ ይገባቸዋል የሚላቸውን ምርጥ ቦታዎች የተመለከቱ ጽሁፎችን በአምዱ ላይ በስፋት ያቀርባል። የወቅቱ ለጉብኝት ተጠቋሚ ቦታ አዲስ አበባ ሆናለች።
ክሪስ “Africa's huge mega-city that's one of the highest capitals in the world” በሚል ርዕስ በጋዜጣው ላይ ባሰፈረው የግል ምልከታ ጽሁፉ ላይ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና በአፍሪካ ከሚገኙ ግዙፍ ሜትሮፖሊታን ከተሞች አንዷ ናት ሲል ገልጿታል።
በፈጣን የዕድገት ጎዳና ላይ የሚገኙት አፍሪካ ከተሞች የዓለምን ቀልብ ስበዋል። ለአብነት ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺህ 355 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው የአፍሪካ መዲናዋ ከተማ ትጠቀሳለች። ይህቺ መዲና ማናት ቢሉ በእንጦጦ ጎረብታ ግርጌ በተራሮችና ገመገሞች ዙሪያዋን ተከባ የምትገኘው አዲስ አበባ ናት።
አዲስ አበባ ለምድር ወገብ የቀረበች ብትሆንም ቅሉ ከፍተኛ ቦታ ላይ በመገኘቷ ዓመታዊ ሙቀቷ በአማካይ 18 ዲግሪ ሴልሺየስ ገደማ ብቻ ነው። ይህም የዓለማችን 4ኛዋ ከፍተኛ ቦታ ላይ የምትገኘው ከተማ ያደርጋታል።
አዲስ አበባ እ.አ.አ በ2025 የህዝብ ብዛቷ ወደ ስድስት ሚሊዮን ይጠጋል። የህዝቡ ቁጥር በየዓመቱ ከአራት በመቶ ላይ እያደገ ይሄዳል። የታዋቂው የምርምር ተቋም ማክሮትሬንድስ መረጃ በዋቢነት አጣቅሷል።
ይህም አዲስ አበባን በአፍሪካ እያደጉ ካሉ ፈጣን ከተሞች አንዷ ከመሆኗ ባሻገር በብዙ መመኛዎች እጅግ ግዙፏ ከተማ እንድትሆን እንዳደረጋት አመልክቷል።
አዲስ አበባ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ የተቆረቆረች፣ እ.አ.አ በ1889 የኢትዮጵያ መዲና የሆነች ከተማ ናት። ከዛ ጊዜ በኋላ ዋንኛ የፖለቲካ፣ ባህል እና ኢኮኖሚ መናኸሪያ ሆናለች።
የብሪሊያንት ኢትዮጵያ የአስጎብኚ ድርጅት ኩባንያ ባለሙያዎች አዲስ አበባ በርካታ ብዝሃ ማንነቶች ያላቸው ህዝቦች እና ዓለዐም አቀፍ ነዋሪዎች የሚገናኙበት ሲል ይገልጻታል።
መዲናዋ ከሀገር በቀል ቋንቋዎች በተጨማሪ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣልያንኛ እና አረብኛም ይወሩባታል።
ክሪስ አዲስ አበባ በርካታ ታዋቂ ስፍራዎች እና የቱሪዝም መዳረሻዎች ያሏት ከተማ መሆኗንም ይገልጻል። በመዲናዋ ሊጎበኙ ይገባቸዋል ያላቸውን ቦታዎችንም በጽሁፉ ላይ ጠቆም አድርጓል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም በብዛት ከሚጎበኙ ስፍራዎች አንዱ መሆኑንና ጎብኚዎች በዓለም ቀደምት ከሚባሉ የሰው ዘር ቅሪተ አካላት መካከል አንዷ የሆነችውን ሉሲን የመጎብኘት እድል ያገኛሉ ሲል ተናግሯል።
ፀሐፊው ሌላ በከተማዋ መጎብኘት አለባቸው ብሎ ካስቀመጣቸው ቦታዎች አንዱ የመስቀል አደባባይ ነው። አደባባዩ የተለያዩ ህዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትን ጨምሮ ለተለያዩ ሁነቶች እንደሚስተናገዱ ገልጸዋል።
መስቀል አደባባይ በመስከረም ወር በክርስትና እምነት ተከታዮች በደማቅ ሁኔታ የተከበረውን የደመራ መስቀል በዓል ማስተናገዱን አውስቷል።
የአዲስ አበባ የከፍታ ጫፍ የሆነው እንጦጦ ተራራ ከባህር ጠለል በላይ የ3200 ሜትር ርዝማኔ አለው። ተራራው የእጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እና የዳግማሚ ምኒሊክ የቀድሞ ቤተ መንግስት ይገኛል።
ቦታው አዲስ አበባን ቁልጭ አድርጎ ለማየት እና ለረጅም የእግር እግር ጉዞ የሚሆኑ መንገዶችን ይዟል።
ተጓዡ ፀሐፊ ቡና በኢትዮጵያውያን ህይወት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያለው መጠጥ እንደሆነ ለመረዳት መቻሉንና በዚህ ረገድም አዲስ አበባ በርከት ያሉ ካፌዎች እና የቡና መጠጫ ስፍራዎች እንዷላት ለመታዘብ መቻሉን ገልጿል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ዋና ገበያ ናት ያላት መርካቶ በአፍሪካ ሰፊው ክፍት ገበያ እንደሆነችም በጽሁፉ ላይ አስፍሯል።
የደራ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደርግባት መርካቶ በህንጻዎች መካከል ባሉ የመተላለፊያ መንገዶች እና በሺዎች የሚቆጠሩ የመሸጫ ቦታዎች ከቅመማ ቅመም ጀምሮ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ሽያጭ ይከናወንባታል ሲል ተናግሯል።
አዲስ አበባ በፍጥነት እየተለወጠች ያለች ከተማ መሆኗን የገለጸው ጉምቱው የጉዞ ፀሐፊ የግንባታ እና የመሰረተ ልማት ስራዎች በመዲናዋ እየተከናወኑ እንደሚገኝ በመግለጽ ሀተታውን ቋጭቷል።