በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ተጠቃሚ መሆን ጀምረናል - አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ተጠቃሚ መሆን ጀምረናል - አርሶ አደሮች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2017(ኢዜአ)፦ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን በምስራቅ ሀረርጌ ዞን የበደኖ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
የፍራፍሬ ልማት፣ የንብ ማነብና የእንስሳት መኖ ምርትና ምርታማነት እያደገ መሆኑንም ገልጸዋል።
አርሶ አደር ኢብሳ አብደላ፥ አካባቢው ተራራማ በመሆኑ አፈሩ በጎርፍ እየተሸረሸረ ለረጅም ዓመታት ተራቁቶ መቆየቱን ገልጸዋል።
በዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች ምርት ለማምረት ይቸገሩ እንደነበር ነው የጠቀሱት።
ችግሩን ለመቅረፍም ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የልማት ሥራ በመግባት የአፈር መሸርሸርን የቀነሰ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
አርሶ አደር አሰን ሸረፍ በበኩላቸው አካባቢው በመልማቱ ምንጮች መጎልበታቸውና ውሃ በቅርበት እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፥ የአካባቢው መልማት ለእንስሳት በቂ መኖ ማምረት እንዳስቻላቸው አንስተዋል።
በዚህ ዓመት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
የበደኖ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ኢብራሂም ዩዬ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ተራቁተው የነበሩ ተራሮች በደን እየተሸፈኑ ናቸው ብለዋል።
በተፋሰስ ልማት የአካባቢው ነዋሪዎች በማህበር ተደራጅተው በፍራፍሬ ልማትና በንብ ማነብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ምርትና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሚስኪ መሀመድ በበኩላቸው፥ ሕዝቡ በሰራው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት የአፈር መከላት እየቀነሰ ለምነት እየጨመረ ነው ብለዋል።
የገፀ እና የከርሰ ምድር የውኃ ምንጮች እየጎለበቱ መሆኑንና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ባህል እየሆነ መምጣቱን ነው ዋና አስተዳዳሪዋ የገለጹት።