በሰሜን ወሎ ዞን እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማቶች የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች በሚመልስ አግባብ እየተከናወኑ ናቸው

ወልዲያ፤መጋቢት 28/2017 (ኢዜአ)፦በሰሜን ወሎ ዞን በወረዳዎችና በከተሞች እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማቶች ለህብረተሰቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጥ አግባብ እየተከናወኑ መሆናቸውን የዞኑ ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያን ጨምሮ በወረዳና ንዑስ የወረዳ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራዎች ወደ ተግባር መግባታቸውን የዞኑ ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያው አስታውቋል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ መኮንን የሱፍ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የኮሪደር ልማቱ ከሚካሄድባቸው ከተሞች ሃራ፣መርሳ፣ፍላቂት፣ጋሸናና ኮን ተጠቃሽ ናቸው።

የእነዚህን ከተሞች የኮሪደር ልማት ለመገንባት መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከህዝብ የተሰበሰበ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማቱ ከተሞችን ለኑሮና ለስራ ምቹ ከማድረጉም በላይ ለህብረተሰቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጡ አግባብ እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ልማቱ ለ350 ስራ አጥ ወገኖች የስራ እድል መፍጠሩን አቶ መኮንን ጠቁመዋል።

በሃራ ከተማ እየተከናወነ ላለው የኮሪደር ልማት ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ያሲን ይማም ናቸው።

ከተማዋን ውብና ጽዱ ለማድረግ የተጀመረውን የኮሪደር ልማትን መደገፍ ለስራ እድል ፈጠራና ለኑሩ ምቹ ለማድረግ ትልቅ እቅም እንደሚፈጥር ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ ከድር ሱልጣን በበኩሉ፥ በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ እንዳስደሰተው ጠቅሶ፥ ከወጣቶች የሚጠበቀውን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

የዞኑ ዋና ከተማ በሆነችው የወልድያ ከተማ ቀድሞ የተጀመረው የኮሪደር ልማቱ በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም