በድሬዳዋ ለመጪው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ ነው

ድሬዳዋ፤ መጋቢት 30/2017(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን የአስተዳደሩ የአካባቢ፣ የደን ልማት እና አየር ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ።

በባለስልጣኑ የደን ልማት ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በዘንድሮ ክረምት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ ናቸው።

በአስተዳደሩ የገጠርና ከተማ ክላስተሮች ችግኝ ጣቢያዎች እየተዘጋጁ ከሚገኙት ችግኞች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከወዲሁ ለተከላ ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል።


 

በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለተከላ እየተዘጋጁ ካሉ ችግኞች መካከል የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ እንደ ሎሚ፣ ፓፓያ፣ ጊሽጣ፣ ማንጎ፣ ሃምበሾክ፣ ብርቱካን እና የመሳሰሉት ይገኙበታል ብለዋል።

እነዚሁ የፍራፍሬና ሌሎች ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለድሬዳዋ አየር ንብረት ተስማሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ችግኝ ተክሎ ማሳደግ ለድሬዳዋ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ማስረሻ፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተተከሉት በርካታ ችግኞች 72 በመቶ መፅደቃቸውንም ተናግረዋል።

ይኸም የጎርፍ አደጋን በመከላከል እና የገጠሩን ማህበረሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መሠረታዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።


 

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ ለኢዜአ እንዳሉት ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ እየተዘጋጁ የሚገኙት ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው።

ችግኞቹ ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ ለደን፣ ለጥላ እና ለከተማ ውበት የሚያገለግሉና በመጠናቀቅ ላይ ለሚገኘው የኮሪደር ልማት ማስዋቢያነት ጭምር የሚውሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በገጠሩ ክላስተርም ችግኞቹ የሚተከሉበትን ስፍራ የመለየትና ጉድጓዶችን ከወዲሁ የማዘጋጀት ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ከማህበረሰቡ ጋርም በመወያየት ከወዲሁ ዝግጁ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም