የተቀናጀ የተፋሰስ አስተዳደር ፕሮጀክት በአባይ፣ አዋሽ እና ተከዜ ተፋሰሶች በይፋ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የተቀናጀ የተፋሰስ አስተዳደር ፕሮጀክት በአባይ፣ አዋሽ እና ተከዜ ተፋሰሶች በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2017(ኢዜአ)፦የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ የሚተገበር የተቀናጀ የተፋሰስ አስተዳደር ፕሮጀክት በአባይ፣ አዋሽ እና ተከዜ ተፋሰሶች በይፋ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ ስነስርዓቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ጌቴ ዘለቀ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የተፋሰስ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች ሀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት መንግስት ለውሃ ሀብት ልማትና ጥበቃ ትኩረት ሰጥቶ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ዛሬ በአባይ፣ አዋሽ እና ተከዜ ተፋሰሶች ይፋ የተደረገው የተቀናጀ የተፋሰስ ፕሮጀክት የውሃ ሀብትን ከመጠቀምና ከመጠበቅ አንጻር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በተፋሰሱ አከባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ ማሻሻልና ለአየር ንብረት ለውጥ ስጋቶች የማይበገር አካባቢን በአስተማማኝ መልኩ እንዲረጋገጥ ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ በኔዘርላንድስና በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበር መሆኑም ተመላክቷል።