በደቡብ ወሎ ዞን ከ29 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን ለመሸፈን የሚያስችል የችግኝ ዝግጅት እየተካሄደ ነው

ደሴ፤ሚያዚያ 1/2017(ኢዜአ)፦በደቡብ ወሎ ዞን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ29 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በደን ለመሸፈን የሚያስችል የችግኝ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ መገርሳ ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

የደን ሽፋንን በማሳደግ፣በተፋሰሶች ለወጣቱ የሥራ እድል በመፍጠር፣ የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ፣ በመኖ ልማት፣ በንብ ማነብና በፍራፋሬ ልማት አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የተገኘውን ጥቅም ለማስፋትም በመጪው ክረምትም ከ29 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በደን ለመሸፈን የሚያስችል ችግኝ ማዘጋጀት መቻሉን ገልጸዋል።

ችግኞቹ የተዘጋጁት በ24 ሺህ 330 የመንግስት፣ በማህበራትና በግለሰቦች ችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች መሆኑንም ገልፀዋል።

ችግኞቹም አብዛኞቹ የፍራፍሬ መሆናቸውን ጠቁመው፥ በተለይም አርሶ አደሩና ወጣቶች ችግኝ አፍልቶ በመሸጥ ከሰብል ልማቱ ባሻገር ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ሀርቡ ከተማ የ01 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሰይድ አህመድ በሰጠው አስተያየት፥ በየዓመቱ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን በማፍላትና በማዘጋጀት በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮም የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ያመጣውን እድል ለመጠቀም ከ75 ሺህ በላይ የማንጎ፣ አቡካዶ፣ብርቱካንና ሌሎችንም የፍራፍሬ ችግኞችን እያዘጋጀ እንደሚገኝ ተናግሯል።

ሌላው የደሴ ዙሪያ ወረዳ የ025 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሉቀን አሊ በበኩላቸው፥ በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ዙሪያ የሚተክሉት የባህር ዛፍ፣ አፕልና ጽድ ችግኞችን እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሚተከሉ ችግኞች ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ ከማስገኘት ባለፈ ምርታማነታችንን ለማሳደግና የደን መመናመንን ለመከላከል አስተዋጽኦው ከፍተኛ በመሆኑ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው ክረምት 30 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ ከተተከለው ችግኝ ውስጥ 80 በመቶው መፅደቅ መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም