በዞኖቹ የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን በማስተዋወቅ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ጽህፈት ቤቶቹ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኖቹ የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን በማስተዋወቅ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ጽህፈት ቤቶቹ

መቱ/ጊምቢ፤ ሚያዚያ 1/2017(ኢዜአ)፡- በኢሉአባቦር እና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችንና ቅርሶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የዞኖቹ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቶች አስታወቁ።
በምዕራብ ወለጋ ዞን ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም ልማትና መድረሻ ቡድን መሪ አቶ ምስጋኑ ደገፋ እንደገለጹት በዞኑ ለቱሪዝም አገልግሎት የሚውሉ በጥናት የተለዩ 206 የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦችና ቅርሶች ይገኛሉ።
ከእነዚህ የቱሪስት መስህቦች መካከል ሰው ሰራሽ ሀይቆች የሆነው ጎሚ ግድብ፤ አባ ሴና ተራራ፣ ኢንቶ ግድብ፣ ሎፒ ጥቅጥቅ ደን፣ ሚኒሲ ፏፏቴና ሌሎቹ ይገኙበታል ብሎዋል።
ዞኑ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ቢኖሩትም እስካሁን ለምቶ የሚፈለገውን ያህል የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ አለመሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ወቅት ግን በዞኑ የተገኘውን ሰለም በመጠቀም የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎቹን በማስተዋወቅ የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚሁ መሰረት በዞኑ ከሚገኙ 206 የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች መካከል በቅርቡ 10 የሚሆኑትን ለማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የኢሉባቦር ዞን ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ደበላ እንደተናገሩት በዞኑ ሰፋፊ የተፈጥሮ ደኖችን ጨምሮ ትላልቅ ፏፏቴዎች፣ ዋሻዎች እንዲሁም ታሪካዊና ባሕላዊ ቱሪዚም መስህቦች ይገኛሉ።
በዞኑ በተለይ በተፈጥሮ ደን መካከል የሚወርዱ 38 ፏፏቴዎች መኖራቸውን ገልጸው ከነዚህም የሶር ፏፏቴ እንደ ሀገርም በትልቅናቱና መስህብነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።
የቱሪስት መስህብ ስፍራዎቹን በአግባቡ በማልማትና በማስተዋወቅ የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ የሚገኙ የሶር ፏፏቴን ጨምሮ የተፈጥሮና በህላዊ ቱሪዝም መስህቦችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ ጥረቱ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።
ዘርፉን በማልማት ሂደት የመንግስትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ህብረተሰቡ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው ብለዋል።