በዞኑ የ22 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የ22 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው

ወልዲያ፤ሚያዝያ 3/2017(ኢዜአ )፦በሰሜን ወሎ ዞን ከ563 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የ22 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ እንደሚገኝ የዞኑ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደሳለ ባዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የመስኖ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ርብርብ እየተደረገ ነው።
በተያዘው በጀት ዓመትም በ563 ሚሊዮን ብር የ22 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ስራ እየተፋጠነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በግንባታ ላይ የሚገኙት የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ 1 ሺህ 115 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ከመንግስት፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ደርጅቶችና ከህብረተሰቡ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እየተገነቡ የሚገኙት ፕሮጀክቶችም በዘጠኝ ወረዳዎች የሚገኙ 3 ሺህ 908 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
የመስኖ ፕሮጀክቶቹ በሚገነቡበት አካባቢ የሚገኘው ህብረተሰብም በጉልበቱ፣በቁሳቁስና በገንዘብ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።
አሁን ላይ የሁለቱ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን የ14ቱ አፈጻጸም እስከ 80 በመቶና የቀሪዎቹ ደግሞ ከ40 በመቶ በላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሁሉንም የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ በዚህ ዓመት አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሃብሩ ወረዳ የቁጥር 4 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞላው አበበ በሰጡት አስተያየት፥ በአካባቢያቸው እየተገነባ የሚገኘው የመስኖ ፕሮጀክት ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን ተዘጋጅተዋል።
በጉባላፍቶ ወረዳ የ018 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አማረ መኩሪያው በበኩላቸው ግንባታው እየተጠናቀቀ በሚገኘው የመስኖ ፕሮጀክት ከግማሽ ሄክታር በላይ የሚሆነውን መሬት መስኖ በማልማት ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።