በክልሉ በህዝቡ ተሳትፎ ከ363 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተከናውኗል

ባህር ዳር፤ሚያዚያ 3/2017 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወራት በህዝቡ ተሳትፎ ከ363 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ማከናወን መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው የተካሄደው ከጥር ወር አጋማሽ እስከ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም ነው።

ለስራውም 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ሰዎችን በመሳተፍ በ8 ሺህ 400 ተፋሰሶች በተፈጥሮ ሃብት መልማታቸውን ገልጸዋል።

ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥም የማሳና የጋራ ላይ ዕርከን፣የውሃ ማስረጊያ ስትራክቸሮች፣ውሃ ማፋሰሻና መቀልበሻ ቦይና የተራቆቱ ተራራማ አካባቢዎችን ከልሎ የመጠበቅ ስራ ይገኙበታል ብለዋል።

ህብረተሰቡ በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ያበረከተው አስተዋፅኦ በገንዘብ ሲተመንም ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳለው ጠቅሰዋል።

ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ የአፈር መከላትን በመቀነስ የሰብል ምርታማነትን መጨመር እንዳስቻለም አስረድተዋል።

የክልሉ ህዝብ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ተግባር የሚያስገኘውን ጥቅም በአግባቡ እየተረዳ መምጣቱንም ጠቁመዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ አርሶ አደር የማታ ቢሰጥ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ የተራቆቱ አካባቢያቸውን ወደ ለምነት እንዲመለስ አስችሏል።

የመሬታቸው ለምነት በመሻሻሉም ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማስቻሉን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ በሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ቀስቃሽ ሳያስፈልገን የአካባቢው ማህበረሰብ በነቂስ በመውጣት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

ቀደም ሲል የተፈጥሮ ሃብት ልማት የተከናወነባቸው ተፋሰሶች በማገገማቸው በንብ ማነብና በእንስሳት ማድለብ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የገለጹት ደግሞ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሙላት መልኬ ናቸው።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ አርሶ አደር የኔው አላምር በበኩላቸው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የተሰራባቸው አካባቢዎች ምንጮች እንዲፈልቁ በማድረጉ በመስኖ ልማት እንዲሳተፉ ምክንያት እንደሆናቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም