ጉባኤው የዌልዲንግ ሥራ በኢንዱስትሪና በሌሎች ትልልቅ ዘርፎች እየተጫወተ ያለውን አበርክቶ ለማስተዋወቅ ያስችላል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2017(ኢዜአ)፦ ሦስተኛው የአፍሪካ የዌልዲንግ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጉባኤና ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ የዌልዲንግ ሥራ በኢንዱስትሪና በሌሎች ትልልቅ ዘርፎች እየተጫወተ ያለውን አበርክቶ ለማስተዋወቅና ግንዛቤን ለማሳደግ ዕድል እንደሚፈጥር ተገለጸ።

ሦስተኛው የአፍሪካ የዌልዲንግ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ ከሚያዚያ 6 እስከ 8 በዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።

በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ማምረትና ብየዳ ልህቀት ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰላሙ ይስሐቅ(ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ ለጉባኤው ዝግጅቶች ተጠናቋል ብለዋል፡፡

በጉባኤው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ16 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ40 በላይ የዌልዲንግ ክህሎት ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት ውድድር እንደሚካሄድም አንስተዋል፡፡

በዊልዲንግ ውድድሩ ከተለያዩ ክልሎች ተወዳድረው የተመለመሉ 21 ተወዳዳሪዎችን ኢትዮጵያ እንደምታሳትፍም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

በዌልዲንግ ላይ ያለው አመለካከት ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው፥ ጉባኤው ዌልዲንግን በተመለከተ ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚያግዝ ነው የጠቀሱት።

ከዚህም በተጨማሪ ዌልዲንግ በኢንዱስትሪና በሌሎች ትልልቅ ዘርፎች እየተጫወተ ያለውን አበርክቶ ማስተዋወቅ ያስችላል ብለዋል፡፡

ልህቀት ማዕከሉ ከተቋቋመበት ግዜ ጀምሮ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና እየሰጠ ሲሆን በተጨማሪም ተኪ ቴክኖሎጂዎችን እያመረተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

በሀገሪቱ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሰሩ የዌልዲንግ ባለሙያዎችን በማፍራት እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን በማምረት በልማት ስራ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ሶስተኛው የአፍሪካ የዌልዲንግ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጉባኤ "አፍሪካን ማብቃት፦ ለክልላዊ ውህደት እና ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የዌልዲንግ አቅምን ማጠናከር” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ኩባንያዎች፣ አምራቾች፣ ምሁራን፣ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች እና ኢንዱስትሪዎች ይሳተፋሉ፡፡

የአፍሪካ የዌልዲንግ ፌዴሬሽን 1ኛ ዓመታዊ ጉባኤን ግብጽ ያስተናገደች ሲሆን ናይጄሪያ ሁለተኛውን ጉባኤ ማዘጋጀቷ ይታወቃል፡።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም