ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2017 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በመጪው መስከረም ወር ሁለተኛውን የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ጉባዔው የሚካሄደው ባለፈው የካቲት ወር በአዲስ አበባ በተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ውሳኔን መሠረት ባደረገ መልኩ መሆኑም ተጠቁሟል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) እና የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ከአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ አካባቢ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በቀጣይ የአውሮፓውያኑ መስከረም 2025 አጋማሽ ላይ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የዝግጅት ሥራዎች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተጠቅሷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ጉባዔው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራ ገልጸዋል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) በበኩላቸው ጉባዔው አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ለመቋቋም በምታደርገው ጥረት ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ጉዳዮች አቅጣጫ ለማስያዝ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።
ስለሆነም ጉባዔው በተሳካ መልኩ እንዲከናወን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ አካባቢ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲም ኢትዮጵያ ጉባዔውን ለማዘጋጀት ያሳየችውን ቁርጠኝነት እና እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶችን አድንቀዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔው በስኬት እንዲጠናቀቅ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።