በ21 ሺህ ተፋሰሶች ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ተከናውኗል -ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በ21 ሺህ ተፋሰሶች ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ተከናውኗል -ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 4/2017(ኢዜአ)፦በ2017 በጀት ዓመት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ እስካሁን በ21 ሺህ ተፋሰሶች ላይ የሥነ አካላዊ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መከናወኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በዚህ ዓመት በአጠቃላይ ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተፋሰስ ልማት ለማልማት በእቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ተፈጥሮን በመጠበቅ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል።
የተፋሰስ ልማቱ የመሬት መሸርሸርን በመከላከል፣የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቋቋም እና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
እንደ አቶ ፋኖሴ ገለጻ በተያዘው በጀት ዓመት በጥቅሉ ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሥነ አካላዊና ሥነ ህይወታዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
የሚለማው ቦታም ከሰው እና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ የማድረግ ሥራ ሌላው ከተያዙ ግቦች መካከል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
እንደ ክልሎች ተጨባጭ ሁኔታ ከ30 ቀናት እስከ 60 ቀናት የተቀናጀ የተፋሰስና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ እስካሁንም በበርካታ አካባቢዎች የእርከን፣ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
በተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ 20 ሺህ 800 ተፋሰሶችን ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን ባለው አፈጻጸም ከእቅድ በላይ በ21 ሺህ ተፋሰሶች መከናወኑን ገልጸዋል።
በለሙ ተፋሰሶች ላይ ከ7 ሺህ በላይ ማህበራት በእንስሳት ማድለብ፣የፍራፍሬ ተክሎችን በማልማት እና በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በእርከን እና ውኃ ማቆር ላይ የተጀመሩ ተግባራትን ተጠናክረዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተፋሰስ ልማት ሥራ ውጤታማ በሆነ መልኩ ከተሰራባቸው አካባቢዎች አንዱ ምስራቅ ሀረርጌ ዞን ነው።
በዞኑ የበደኖ ወረዳ አርሶ አደር አህመድ ነጃሺ ከዚህ በፊት ተራቁቶ የነበረው መሬት እሁን እርጥበት መያዝ በመጀመሩ ምርት በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተፋሰስ ልማት ሥራው አሁን ላለው ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ አካባቢን ተንከባክቦ ለማስረከብ ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ በትኩረት እየተሳተፉበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የጎሮ ጉቱ ወረዳ አርሶ አደር ኃይሌ ታደሰ በበኩላቸው በተፋሰስ ልማቱ የተለያዩ ፍራፍሬ በማምረት እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸዋል።
የተፋሰስ ልማቱ በአካባቢው የነበሩ ምንጮች አገግመው በቂ ውሃ እየሰጡ ነው ብለዋል።
ሌላው የወረዳው አርሶ አደር እሸቱ አሰፋ በበኩላቸው፥ በተፋሰስ ስራ ባለሙት መሬት ላይ የተለያዩ ችግኞችን በመትከል እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸዋል።