በዞኑ የሚገኙትን ማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ደኖች በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችል ምክክር ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የሚገኙትን ማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ደኖች በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችል ምክክር ተካሄደ

ደብረብርሀን ፤ሚያዚያ4/ 2017(ኢዜአ)፡- በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙትን የወፍ ዋሻና የመንዝ ጓሳ ማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ደኖችን በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችል የ10 ዓመት አስተዳደራዊ እቅድ ምከክር ተካሄደ።
የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው የአማራ ክልል አካባቢና ደን ባለስልጣን "ዊፎረስት ኢትዮጵያ" ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው።
የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ ተሾመ አግማስ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ጥብቅ ደኖችን በመንከባከብና በማልማት ወደ ብሔራዊ ፓርክነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
ጥብቅ ደኖችን ወደ ብሔራዊ ፓርክነት በማሳደግም ለዘመናት በመጠበቅና በመንከባከብ የኖረውን ማህበረሰብ ከደን ልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙትን የጣርማ በርና የወፍ ዋሻ ጥብቅ ደኖችን ወደ ብሔራዊ ፓርክነት ለማሳደግ የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም የ10 ዓመት አስተዳደራዊ እቅድ በማዘጋጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ተዘጋጅቶ በዛሬው እለት ለምክክር መቅረቡን አስገንዝበዋል።
ይህም በደኖቹ ውስጥ ያሉ እንስሳት፣ እጽዋትና ሌሎች ሃብቶችን ለምርምር በማዋልና የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን በመሳብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ደኖቹ የካርቦን ልቀትን በመከላከል ለአለም የሚያበረክቱትን በጎ አስተዋጽኦ በማስጠናት ከካርቦን ሽያጭ የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ደን ልማት የሬድ ፕላስ ፕሮግራሞ አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ በማስቻል የስነ ምህዳር ጥበቃው እንዲሻሻል አስችሏል ብለዋል።
የዛሬው የውይይት መድረክም ጥብቅ ደኖቹን በማልማትና በመንከባከብ አገራችንን በቱሪዝም ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።
ዊ ፎረስት ኢትዮጵያ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር አክሊሉ ንጉሴ (ዶ/ር) እንዳሉት በተለይም በወፍ ዋሻ ጥብቅ ደን ውስጥ ለጥናትና ምርምር የሚውሉ እድሜ ጠገብ ደኖች ይገኛሉ ብለዋል።
ከመንግስት ጋር በመተባበር እምቅ ጸጋ ያለውን ጥብቅ ደን ወደ ብሔራዊ ፓርክነት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ 10 ዓመታት ከወፍ ዋሻ ጥብቅ ደን የካርቦን ሽያጭ ተጠቃሚ በመሆን የአገራችን ኢኮኖሚ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አመልክተዋል።
ከ1954 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት ጥብቅ ደን ሲተዳደር የቆየው የወፍ ዋሻ ጥብቅ ደን በ15 ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን 8 ሺህ 739 ሄክታር መሬትን እንደሚሸፍንም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።