ኮሌጁ ተወዳዳሪ የሰው ኃይልን በማፍራት የአካባቢውን እንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እየደገፈ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮሌጁ ተወዳዳሪ የሰው ኃይልን በማፍራት የአካባቢውን እንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እየደገፈ ነው

ደብረብርሀን፤ ሚያዚያ 4 / 2017(ኢዜአ) ፡-የደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይልን በማፍራት በአካባቢው እያደገ የመጣውን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ለመደገፍ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ።
ኮሌጁ "ብሩህ አዕምሮዎች በክህሎት የበቁ ዜጎች" በሚል መሪ ሃሳብ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂና የጥናትና ምርምር ስራዎች ውድድር አካሄዷል።
የደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ባሻዬ በየነ እንደገለጹት የአገራችን ኢኮኖሚ የሚፈልገውን በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማምረት ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚጠበቅ ነው።
በአሰልጣኞች፣ በሰልጣኞችና በኢንተርፕራይዞች ደረጃ የተካሄደው ቴክኖሎጂን የመቅዳት፣ የማላማድና የማሸጋገር ውድድር በቀጣይ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
ይህም ለአገራችን ኢኮኖሚ ውጤታማ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው የሚቀርቡ ተወዳዳሪዎችን በመለየትና እውቅና በመስጠት በቀጣይ ለህብረተሰብ ጥቅም እንዲውሉ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም አሰልጣኞች፣ ሰልጣኞችና ኢንተርፕራይዞች እርስ በእርስ በመተዋወቅ፣ ተሞክሮ በመለዋወጥና በቅንጅት በመስራት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገሩ እድልን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የማኑፋክቸሪንግ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ህይወት አስናቀ እንደገለጹት ኤሌክትሪካል የወተት መናጫ ማሽን በመስራት ለውድድሩ መቅረባቸውን ተናግረዋል።
ያቀረቡት ቴክኖሎጂም በ20 ደቂቃ ውስጥ ወተቱን በመናጥ ጥራት ያለው ቅቤ ለማምረት የሚያስችል ነው።
የዌብ ዴቨሎፕመንትና ዳታ ቤዝ አድሚኒስትሬሽን ሰልጣኝ የሆነው ባየሁ ገበየሁ በበኩሉ ባለብዙ ልኬት የአፈር መመርመሪያና መረጃ ማከማቸት የሚችል ቴክኖሎጂ ይዞ በመቅረቡ ለአሸናፊነት መብቃቱን ተናግሯል።
ቴክኖሎጂው የአፈሩን የማዕድን ዓይነት፣ ሙቀት፣ ርጥበትና አሲዳማነት በመለየትና መሬቱን በማከም ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን አስረድቷል።
ከኢንተርፕራይዞች መካከልም አቶ ኢያሱ ገረመው እንደገለጸው ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ ሸንብራና ጤፍን በቀን እስከ 200 ኩንታል መውቃት የሚችል ማሽን ለውድድር ይዞ መቅረቡን አስረድቷል።
ከውጭ እስከ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ ይገባ የነበረውን የእህል መውቂያ ማሽን ከ400 ሺህ ብር ባልበለጠ ዋጋ ለአርሶ አደሩ የሚቀርብ በመሆኑ አዋጭ ነው ብለዋል።
በደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተዘጋጀው የቴክኖሎጂ ውድድር ላይም በዞኑ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተወዳዳሪነት መሳተፋቸውም ተመላክቷል።