ከሞጆና ሉሜ አካባቢዎች የችግኝ ዝግጅትና የተቀናጀ የግብርና ሥራዎች የልምድ ልውውጥ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ከሞጆና ሉሜ አካባቢዎች የችግኝ ዝግጅትና የተቀናጀ የግብርና ሥራዎች የልምድ ልውውጥ ተደረገ

አዳማ ፤ ሚያዝያ 4/2017(ኢዜአ)፡- በምስራቅ ሸዋ ዞን ሞጆና ሉሜ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የችግኝ ዝግጅትና የተቀናጀ የግብርና ሥራዎች የልምድ ልውውጥ መረሐ ግብር ተካሄደ።
ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተወጣጡ የግብርና ዘርፍ አመራር አባላት በምስራቅ ሸዋ ዞን የችግኝ ጣቢያዎችና አቮካዶ ክላስተር እንቅስቃሴን በሞጆና ሉሜ አካባቢዎች ተገኝተው ተመልክተዋል።
በዘህ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የሐረር ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ነስረዲን አህመድ በሰጡት አስተያየት፤ በሞጆ ያየነው የችግኝ ጣቢያ የተደራጀና የተቀናጀ ሳይት ነው ብለዋል።
በጣቢያው ከሚከናወነው የችግኝ ዝግጅትና የተቀናጀ የግብርና ሥራ በተለይ የአቮካዶ ልማት፣ንብ ማነብና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት በአንድ ማዕከል እየተከናወነ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።
በዚህም መልካም ተሞክሮና ልምድ ያገኙበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ተሞክሮ ወደ ክልላችን ወስደን እንስፋፋለን ሲሉም ገልጸዋል።
በአፋር ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የባዮ ዳይቨርሲቲ ዳይሬክተር አቶ አሊ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ከሞጆና ሉሜ አካባቢዎች የችግኝ ዝግጅትና የተቀናጀ የግብርና ሥራ ልምድና እውቀት ያገኘንበት ነው ብለዋል ።
በተለይ በመስኖ ለምግብነትና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ችግኞችን ማዘጋጀት እንደሚቻል መረዳታቸውን ጠቅሰው፤ በክልሉ ጨዋማና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ አቮካዶን ጨምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የመጡት አቶ በየነ በላቸው በበኩላቸው፤ የሞጆ ችግኝ ጣቢያና የአቮካዶ ክላስተር በእውቀትና ክህሎት የተዘጋጀ መሆኑን ከምልከታቸው እንደተረዱ ገልጸዋል።
በተለይ አቮካዶ ከማምረት ባለፈ የአቮካዶ ችግኝ ወደ ውጭ ለመላክ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ ክልላችን ለአቮካዶ ልማት አመቺ በመሆኑ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የአቮካዶ ዝሪያዎች ከኦሮሚያ ክልል ገዝተን የማዳቀል ስራ እየሰራን ነው ብለዋል።
የሉሜ ወረዳ ምክትል አስተዳደሪና የግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ለሚ ይርኮ ፤ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መረሐ ግብር በፍራፍሬና የእንስሳት መኖ ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በዚህም ሞጆን ጨምሮ በወረዳው 150 የችግኝ ጣቢያዎች ላይ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላቸው 35 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ለ4ኛ ጊዜ የአቮካዶ ምርት ከወረዳው በማዕከላዊ ገበያ በኩል ወደ ውጭ መላኩን ጠቁመው፤ በተጨማሪ የተሻሻሉ የአቮኮዶ ችግኞችን ወደ ውጭ ለመላክ ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን በበኩላቸው፤ የመስክ ምልከታው በመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መረሐ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ዝግጅት በመሬት ላይ ያለውን የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደተሰናዳ ገልጸዋል።
በተለይ የሞጆ ችግኝ ጣቢያ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ችግኞች ዝግጅት ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ፋኖሴ ፤ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ዝግጅት 60 በመቶ የፍራፍሬ፣ የእንስሳት መኖና ለውበት የሚውሉ ሲሆን፤ 40 በመቶ ለደን ልማት ነው ብለዋል።