ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በቻይና የሁዋዌ ቴክፎርጉድ ግሎባል ውድድር አሸነፉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በቻይና የሁዋዌ ቴክፎርጉድ ግሎባል ውድድር አሸነፉ

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 4/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ቴክ ፎር ጉድ ግሎባል ውድድር አንደኛ በመውጣት አሸንፈዋል።
በስድስት ተማሪዎች የተወከለው የኢትዮጵያ ቡድን ተማሪዎቹን ከአዲስ አበባ፣ ሃረማያ፣ ጅማ፣ ወልቂጤ እና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች ያካተተ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በውድድሩ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ፤ አርጀንቲና፣ አየርላንድ፣ ማላዊ፣ ቬትናም፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሌሎችንም ጨምሮ ከዓለም ዙሪያ ከተውጣጡ 12 ልዩ ቡድኖች ተወዳድረዋል።
የሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ግሎባል አምባሳደር የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ ተማሪ አሲያ ከሊፋም በዝግጅቱ በእንግድነት ተገኝታለች።
ተማሪዎቹ የእንስሳትን ህመሞች አስቀድሞ ለመለየት በተዘጋጀውና በአርተፊሻል አስተውሎት በጎለበተው ኤርሊ ቬት (EarlyVet) በተሰኘው ፕሮጀክታቸው የተወዳደሩ ሲሆን በዚህም ትኩረት ለመሳብ ችለዋል።
ፈጠራ ፕሮጀክቱ ከተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦችበተለይም ግብ 2 "ዜሮ ርሃብ" እና ግብ 15 "ህይወት በምድር" ከሚለው ጋር የተጣጣመ መሆኑና በግብርና እና በእንስሳት ጤና ላይ ያሉ ወሳኝ ተግዳሮቶችን ይፈታል ተብሎ እምነት ተጥሎበታል።
የሁዋዌ ኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሚስተር ሊሚንግ ዬ በቡድኑ ስኬት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ድሉ የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ልዩ ችሎታ እና ፈጠራ የታየበት ነው ብለዋል።
ሁዋዌ መጪው በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለሚከናወኑ ስራዎች ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
ቡድኑ ለዓለም አቀፋዊ ውድድር እድል ያገኘው በግንቦት 2016 ዓ.ም በኤሳውራ ሞሮኮ በተካሄደው የክፍለ አህጉራዊ የቴክፎርጉድ (Tech4Good) ውድድር ወቅት ከ17 የአፍሪካ ሀገራት ከተውጣጡ 28 ቡድኖች ጋር ተወዳድሮ አንደኛ በወጣበት ወቅት ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ. በ2008 የተጀመረው የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ፕሮግራም በአገር ውስጥ ያለውን ውድድር ከኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጃል።
ለተሳታፊ ተማሪዎች ከውድድር ባለፈ የሰዉ ሰራሽ አስተዉሎት (AI)፣ ክላዉድ ኮምፒዉቲንግ፣5ኛ ትውልድ፣ ሳይበር ደህንነት እና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ላይ አጠቃላይ ስልጠና የሚወስዱበት እድል እንደሚያመቻች የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።