ዲጂታል የአሰራር ስርዓትን በማስፋትና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል- ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል የአሰራር ስርዓትን በማስፋትና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል- ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 5/2017(ኢዜአ)፦በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ዲጂታል የአሰራር ስርዓትን በማስፋትና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የተሻለ ስራ መከናወኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።
የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።
ሚኒስትሩ የዘርፍ አፈጻጸምን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ዲጂታላይዜሽንን በማስፋት እንዲሁም መሰረተ ልማቶች እንዲጠናከሩ በማድረግ በኩል ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም ከገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ 800 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በዲጂታል መንገድ መዘዋወሩን ጠቅሰው፤ ይህም በዲጂታል ስነምህዳር ውስጥ ትልቅ እመርታ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን አንስተዋል።
የመሰረተ ልማት ዝርጋታን በተመለከተም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከፍተኛ ስራ መከናወኑን ገልጸው፤ በዚህም የኢንተርኔት እና የሞባይል ተጠቃሚ የማህበረሰብ ክፍል እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በተያያዘም እስከ አሁን 14 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ምዝገባ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።
ይህም ከእቅዱ አንጻር መልካም የሚባል እና በቀጣዮቹ ጊዜያትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል።
ከሰው ሀብት ልማት ጋር በተያያዘም በ5 ሚሊዮን ኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ እስከ አሁን 688 ሺህ ኢትዮጵያውያን ተመዝግበው ስልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከነዚህም 270 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አለም አቀፍ ሰርቲፊኬት ማግኘታቸውን አመላክተዋል።
ይህም ትልቅ እድል መሆኑን ጠቅሰው፤ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን አንስተዋል።
በአጠቃላይ ዲጂታል የአሰራር ስርዓት በማስፋትና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የተሻለ ስራ መከናወኑን አብራርተዋል።