በጉጂ ዞን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለመጪው ክረምት ተከላ ተዘጋጅተዋል

አዶላ፤ ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ)፦ በጉጂ ዞን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለመጪው ክረምት ተከላ መዘጋጀታቸውን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ቡድን መሪ አቶ ወንዶ ሸርቦቴ እንዳሉት እስካሁን በዞኑ 13 ወረዳዎች በተካሄደው ስራ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡


 

በዞኑ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል የፍራፍሬ፣ የደን፣ የጥላ ዛፍ፣ የእንስሳት መኖና የቡና ችግኝ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

ሃላፊው እንዳሉት ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚውሉ በዋናነት የቡና፣ አቦጋዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ ዘይቱን የሚጠቀሱ ሲሆን፤  ለደንነት ደግሞ የሀበሻ ጽድ፣ ዋንዛና ኮሶ፣ በብዛት ቀዳሚዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡

ከነዚህም ሌላ የውበት የጥላ ዛፍና የእንስሳት መኖ የመሳሰሉት በችግኝ ዝግጅቱ ውስጥ የተካተቱ እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡

ከዚህም ጎን ለጎን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ የተራቆተን 21 ሺህ ሄክታር በላይ የችግኝ መትከያ መሬት እየተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተከላ ስራው በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች 184 ሺህ በላይ የሚገመት የዞኑ ህዝብ ይሳተፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል፡፡


 

በዞኑ አዶላ ወረዳ የደራርቱ ቀበሌ ነዋሪና አባገዳ ኦዳ ጎበና አንድ ዛፍ ሲቆረጥ 10 ችግኝ መትከል የተለመደው የገዳ ባህል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በአከባቢ መራቆትና በደኖች መመናመን ባለፉት ዓመታት በአከባቢያችን ከተከሰተው ድርቅ ብዙ ነገር ተምረናል ያሉት አባ ገዳው፤ ይኸንን ለመቀልበስ የሚያስችሉ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ሥራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።፡

ችግኝ ማዘጋጀትና መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ማሳደግም ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እያስተማሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የዚሁ ወረዳና ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ጎበና ዱከሌ ችግኝ ተክሎና ተንከባክቦ ማሳደግ ከማንም በላይ የእኛ የወጣቶች ድርሻ ነው ብሏል፡፡

አከባቢን መንከባከብ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ባለፉት ዓመታት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ከተከናወኑ የልማት ስራዎች ትምህርት መወሰዱን ያስታውሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም