ኢትዮጵያውያን ሀሳብ አፍላቂዎች በግዙፉ የቴክኖሎጂ ሁነት ላይ ስራቸውን ያቀርባሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ሀሳብ አፍላቂዎች በግዙፉ የቴክኖሎጂ ሁነት ላይ ስራቸውን ያቀርባሉ

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ)፦በአፍሪካ ግዙፉ የቴክኖሎጂ እና የጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች (ስታርትአፕ) ሁነት እንደሆነ የሚነገርለት 3ኛው ጂአይቴክስ አፍሪካ የቴክኖሎጂ መድረክ ዛሬ በሞሮኮ ማራካሽ ተጀምሯል።
መድረኩ በአፍሪካ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ኢኖቬሽን እና የቢዝነስ ትስስር የመሪነት ስፍራ ላይ የተቀመጡ ተቋማት እና ግለሰቦችን ያገናኘ ነው።
በሁነቱ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ130 ሀገራት በላይ የተወጣጡ ከ4 ሺህ 500 በላይ ተወካዮች፣ከ1 ሺህ 400 በላይ ስራቸውን የሚያቀርቡ ኩባንያዎች እና ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች፣ከ650 በላይ የመንግስት ተቋማት እና ከ350 በላይ ባለሀብቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
ሳይበር ደህንነት፣ ትምህርት፣ ቴሌኮም፣ ፋይናንስ፣ ጤና፣ ስፖርት እና የግብርና ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና ግለሰቦች ከሚያቀርቧቸው የቴክኖሎጂ ስራ ፈጠራዎች መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ።
በአህጉራዊው የቴክኖሎጂ መድረክ የማህበረሰብን ችግር የሚፈቱ እና ህይወትን የሚያቀሉ ተጨባጭ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር የቻሉ ኢትዮጵያውያንም ተሳታፊዎች ናቸው።
ኢትዮጵያውያኑ በሁነቱ ላይ ስራቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ሳይበር ደህንነት፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ ዘላቂ ልማት፣ ስራ ፈጠራ እና ሌሎች ተጓዳኝ ጉዳዮች ላይ የጎንዮሽ ውይይቶች ይካሄዳሉ።
የ2025 የጂአይቴክስ አፍሪካ መድረክ ለአፍሪካ ልማት እና ዲጂታል ሽግግር ትኩረት የሚሰጥ እና አፍሪካ የዓለም የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ስራዎች ማዕከል ለማድረግ የሚሰራ ነው።
በሞሮኮ ማራከሽ እየተካሄደ የሚገኘው መድረክም በአህጉሪቱ ያሉ ምርጥ አዕምሮዎችን በማሰባሰብ እና የእውቀት ሽግግር እንዲሳለጥ በማድረግ አፍሪካ በዓለም የቴክኖሎጂ ውድድር የመሪነቱን ቦታ እንድትይዝ አይነተኛ ሚና የሚጫወት ነው ተብሎለታል።
ዲጂታል ኢኮኖሚ ለአፍሪካ ዓመታዊ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) ከ180 ቢሊዮን ዶላር በላይ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ እና የአህጉሪቷ የሳይበር ደህንነት ገበያ በዓመት የ245 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የማመንጨት አቅም እንዳለው ተገልጿል።
ጂአይቴክስ አፍሪካ እስከ ሚያዚያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ የኢዜአ ሪፖርተር ከስፍራው ዘግቧል።
የቴክኖሎጂ ሁነቱ በሞሮኮ ንጉስ መሐመድ ስድስተኛ የበላይ ጠባቂነት የሚመራ ነው።