ቤላሩስ ለኢትዮጵያ በባለብዝሃ ወገን መድረኮች ላይ የምትሰጠውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ):- ቤላሩስ ለኢትዮጵያ በባለብዝሃ ወገን መድረኮች ላይ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክር እንድትቀጥል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በቤላሩስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሲም ራይዜንኮቭ ከተመራ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ውይይቱ ሁለቱ ሀገራት በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽን፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በሰው ሀብት ልማትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።

ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ ቤላሩስ በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ለኢትዮጵያ ለሰጠችው ድጋፍ እና ላሳየችው የገለልተኝነት አቋም ምስጋናቸውን አቅርበው ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና በሌሎችም ዘርፎች በስፋት እየሰራችና አበረታች ውጤት እያስመዘገበች ይገኛል ብለዋል።

በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ ከአጋር ሀገራት ጋር የምታደርገውን የትብብር ስራዎች ይበልጥ ትኩረት እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ተወዳዳሪነትን በማጠናከር የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር በመሰረተ ልማት፣ በሰው ኃይል ግንባታና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤትነት ላይ ስኬታማነትን እንድታረጋግጥ የአጋር ሀገራት ትብብር ወሳኝ ሚና እንዳለውም ነው ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት።

የቤላሩስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሲም ራይዜንኮቭ በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመስራትና ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

በተለይም በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በማዕድን፣ በንግድ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በሌሎች ዘርፎች ላይ ከኢትዮጵያ የሚቀርቡ የአጋርነት ፍላጎቶችን በመንተራስ በትብብር ለመስራት ዝግጁ ናት ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ቤላሩስን እንዲጎበኙም ጋብዘዋል።

የሁለትዮሽ ምክክሩ የሀገራቱን ትብብር ለማጠናከርና በተመረጡ ዘርፎች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ቀጣይነት ያለው ውይይት ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም