ኢትዮጵያ በቴክኒክ ሙያ ዘርፍ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቴክኒክ ሙያ ዘርፍ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 6/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሶስተኛው የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌደሬሽን ጉባኤ በአዲስ አበባ ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው ላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት የቴክኒክ ሙያ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት መሰረት በመሆኑ ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች፡፡
የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ክህሎት ላይ መሰረት ያደረገ እውቀት ወሳኝ በመሆኑ መንግስት የስራና ክህሎት ሚኒስቴርን ጨምሮ የቴክኒክና ሞያ ማሰልጠኛ ተቋማትን በማጠናከር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ለቴክኒክና ሞያ በተሰጠው ትኩረት በዘርፉ የሰለጠኑ በርካታ ሞያተኞች በኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት ምቹ ሆኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ አገራትም በቴክኒክ ሙያ ዘርፍ ያላቸውን የሰው ሀይል፣ እውቀት እና ልምድ በመለዋወጥና በጋራ በመስራት እርስ በእርስ መማማር እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ በአፍሪካ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ለማሳደግ ከሀገራት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሐመድ አብደል-አሊም በበኩላቸው የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌዴሬሽን በስድስት ዓመታት ውስጥ ከ13 በላይ አባል ሀገራትን ለማፍራት በቅቷል ብለዋል።
የዌልዲንግ ዘርፍን በቀጣይ ለማሳደግ በሀገራት የኢንዱስትሪ ስትራቴጂዎችና በሙያ ትምህርት ስርዓቶች ውስጥ ማካተት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በሰው ሀይል ላይ ኢንቨስት ማድረግና የስልጠና መሰረተ ልማቶችን ማሻሻል ወሳኝ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ አመልክተዋል ።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) በበኩላቸው የዌልዲንግ ቴክኖሎጂ የዘመናዊ ኢንዱስትሪ መሰረት በመሆኑ ኢትዮጵያ በዘርፉ የልህቀት ማዕከል አቋቁማ በርካታ ተግባራት እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።
ዌልዲንግ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጨማሪ የስራ እድል በመፍጠር በኩል ትልቅ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የዌልዲንግ ሙያ የበለጠ ተፈላጊና ተወዳዳሪ እንዲሆን በኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚጫወተውን ሚና ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ሶስተኛው የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌዴሬሽን ጉባኤና አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ ያላትን ተሞክሮ እንድታካፍል እና ልምድ ልውውጥ እንድታደርግ የሚያግዝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ናቸው ፡፡
16 የአፍሪካ አገራት እየተሳተፉበት የሚገኘው ጉባኤው ዛሬን ጨምሮ እስከ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ድረስ እንደሚቆይም ተገልጿል።