በክልሉ የተፋሰስ ልማት ስራ በግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ ውጤት አምጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተፋሰስ ልማት ስራ በግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ ውጤት አምጥቷል

አዳማ፤ሚያዝያ 7/2017(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የተፋሰስ ልማት ስራ የአካባቢውን ስነ ምህዳር ከማስጠበቅ ባለፈ በግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ከድር ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ ከጥር 15/2017 ዓም ጀምሮ እየተከናወነ ነው።
በህዝቡ ንቅናቄ የተጀመረው የተፋሰስ ልማት ስራ ሳይንሳዊ አሰራርን ተከትሎ እንዲከናወን ከክልሉ ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች ድጋፍና ክትትል ሲያደርጉ ነበር ብለዋል።
በክልሉ 6 ሺህ 400 ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚሸፍን የተፋሰስ ልማት ስራ ለ60 ቀናት በህዝብ ንቅናቄ መከናወኑንም ገልጸዋል።
በዚህም በርካታ የክልሉ ህዝብ መሳተፉን የገለፁት አቶ ኤሊያስ፤ ''የአካባቢውን ስነ ምህዳር ጠብቀን ለትውልድ ለማስተላለፍ መሰረታዊ ስራዎች እየተሰራ ነው'' ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች ደርቀው የነበሩ የሀሮማያና ጨርጨርቅ ሐይቅን ጨምሮ ወንዞችና ዥረቶች የተመለሱ ሲሆን አሁን ላይ ለመስኖ ልማት አገልግሎት እየዋሉ ይገኛሉ ብለዋል።
እንዲሁም በተፋሰስ ልማቱ በቡና፤ በፍራፍሬ፤ በደን ልማት፤ በሰብል ልማትና በስነ ምህዳር ጥበቃ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ሲሉም ገልጸዋል።
''በተመሳሳይም የአየር ጠባይ ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋምና ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ በተሰራው የተፋሰስ ልማት ስራ የአፈር መሸርሸርና መከላት መቀነስ ችለናል'' ብለዋል።
በዘርፉ ለወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል አማራጭ መሆኑን የገለፁት ምክትል ሃላፊው በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ፤ በእንስሳት መኖ፤ በንብ ማነብና ማር ልማት፤ በእንስሳት እርባታና ማድለብ በባለቤትነት ተረክበው እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ ከ670 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከንኪኪ ነፃ ተደርጎ እንዲያገግም እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።