በክልሉ የቴክኖሎጂ ክህሎታቸው የዳበረ ዜጎችን መፍጠር ቀዳሚ አጀንዳ ነው-አቶ ጥላሁን ከበደ

አርባ ምንጭ፤ሚያዚያ 7/2017 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኖሎጂ ክህሎታቸው የዳበረ ዜጎችን መፍጠር ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡

ክልል አቀፍ የኢትዮ-ኮደርስ ኢኒሼቲቭ አፈጻጸም ግምገማና ንቅናቄ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፥ የቴክኖሎጂ ክህሎታቸው የዳበረ ዜጎችን መፍጠር የክልሉ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ እየተሰራ ነው።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትኩረት ከተሰጣቸው ብዝሃ ዘርፎች አንዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሆኑን አስታውሰው፥ፕሮጀክቱ የብልጽግናን ራዕይ ለማሳካት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

ሀገራት እድገት ያስመዘገቡት በቴክኖሎጂ ወደፊት በመሄዳቸው መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ኋላቀርነትና ድህነትን ማስወገድ የምንችለው በቴክኖሎጂ የዳበረ ክህሎት ያላቸውን ዜጎች መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው ብለዋል።

ኢትዮ ኮደርስ ዜጎችን በቴክኖሎጂ ክህሎት በማበልጸግ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከማድረግ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራ በር የሚከፍት ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል።

የኮደርስ ስልጠና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም መንግስት ዜጎች ስልጠናውን በነፃ እንዲያገኙ ማመቻቸቱ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።

የክልሉ የኮደርስ ስልጠና አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ዜጎች ይህን ዕድል በመጠቀም ራሳቸውን ከዘመኑ ጋር ሊያራምዱ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ እንዲሁም የኢትዮ ኮደርስ ስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ በበኩላቸው የኢትዮ ኮደርስ ኢንሼቲቭ ለነገ የሀገር ተረካቢ ትውልድ የምንፈጥርበት ልዩ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

በክልሉ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት እስከ 60 ሺህ ዜጎችን በኮደርስ ለማሠልጠን ታቅዶ እስካሁን ድረስ 38 ሺህ ዜጎችን ማሠልጠን እንደተቻለ ተገልጿል።

ከእነዚህም 6 ሺህ የሚሆኑት ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ነው የተናገሩት።

አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ የድጋፍና ክትትል ስራውን በማጠናከር ለክልሉ የተሰጠውን ዕድል አሟጦ ለመጠቀም እንደሚሰራ ገልጸው፣ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንድወጡ ጠይቀዋል።

በመድረኩ ላይ የኢትዮ ኮደርስ አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም