ኢትዮ ኮደርስ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በማስታጠቅ የአሰራር ስርዓትን ያዘምናል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ኮደርስ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በማስታጠቅ የአሰራር ስርዓትን ያዘምናል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

አርባ ምንጭ፤ ሚያዚያ 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮ ኮደርስ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በማስታጠቅ የአሰራር ስርአትን የሚያዘምን በመሆኑ ለስኬታማነቱ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አስገነዘቡ።
ክልል አቀፍ የኢትዮ-ኮደርስ ኢንሼቲቭ አፈጻጸም ግምገማና የንቅናቄ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በወቅቱ እንዳሉት ዲጂታል ማህበረሰብን መፍጠር የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት ትልቅ መሣሪያ በመሆኑ የኢትዮ-ኮደርስ ፕሮጀክትም ለስኬቱ አጋዥ ነው።
ይህን እውን ለማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮች ብቃት ያለው አመራር መስጠት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ኢትዮ ኮደርስ ስልጠናም ዘመኑን የዋጀ የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎትን በመዘርጋት የአሰራር ስርዓትን ለማዘመን ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
አገልግሎቱን ትልቅ መሠረተ ልማትን መገንባት ሳያስፈልግ በእጅ ባሉ ስልኮችና ኮምፒውተሮች ብቻ የዲጂታል እውቀትን በማዳበር ማህበረሰብን ማገልገል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ሳይንስ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተካልኝ ጋሎ በበኩላቸው ኢትዮ ኮደርስ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የማይተካ ሚና ስላለው ቢሮው ይህን ለመተግበር እየሰራ ነው ብለዋል።
ወጣቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና የሥራ ባለቤት እንዲሆንና ሁለንተናዊ ሀገራዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑንም ገልፀዋል።
ለተግባራዊነቱም ክልሉ በሶስት ዓመታት ከ235ሺህ በላይ ዜጎችን ተሳታፊ ለማድረግ በየዓመቱ ከ58ሺህ በላይ ዜጎችን የዕድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ህይወትና አኗኗር ከማቅለልና ዲጂታል ማህበረሰብን ከመፍጠር አኳያ ድርሻው ጉልህ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አብደላ ከማል(ዶ/ር) ናቸው።
ያለ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የአንድ ሀገር ዕድገት ሊረጋገጥ የማይችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው የኢትዮ-ኮደርስ ፕሮጀክት ዕቅድ እንዲሳካ የበኩሉን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲኖች፣ የዞን ዋና አስተዳዳሪዎች፣ የመንግስት ተጠሪዎች፣ ከንቲባዎችና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።