አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን መቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባት ይኖርብናል - የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን መቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባት ይኖርብናል - የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 7/2017(ኢዜአ)፦አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ሁሉን አቀፍ አቅም መገንባት ይኖርብናል ሲሉ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።
የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት 24ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን ዛሬ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።
ምክር ቤቱ በስብሰባው የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት የአንድ አባል ምርጫ ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል።
በተመሳሳይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የዓለም አቀፍ ህግ አማካሪ አደረጃጀት (AUCIL) አንድ አባል እንዲሁም የአፍሪካ የህዋ ምክር ቤት (AfSC) አንድ አባል ምርጫ ይከናወናል ።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ልማት፣ ቱሪዝም፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽን እና የትምህርት ፣ሳይንስ ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር የምርጫ ሂደት አስመልክቶ የተዘጋጀ ረቂቅ ሪፖርት ያዳምጣል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የአፍሪካ አህጉር በርካታ ውስብስብ ችግሮች እየገጠሙት ይገኛል።
የአንዳንድ እርዳታ ሰጭ ተቋማት ድጋፍ መቋረጥ በጤናና በምግብ ዋስትና ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን ጠቅሰው፤ አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን መቋቋም የሚያስችል ሁሉን አቀፍ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የመሳሰሉ ዘዴዎችን ለመተግበር በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
የአንጎላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የወቅቱ የምክር ቤቱ ሊቀ-መንበር ቴቴ አንቶኒዮ በበኩላቸው፤ ሰላም እና መረጋጋት ለእድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
አህጉራዊ ተቋማት የሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮችን ለመቋቋም የሚያስችል ጠቃሚ ግብዓት እንዳላቸው ጠቁመው፤ ይህም የውሳኔ ሰጭውን አካል መፍትሄ የሚፈለግ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህብረት እነዚህን ተግዳሮቶች በጥበብ እና አርቆ አስተዋይ አመራር በመምራት ረገድ ንቁ መሆን አለበት ያሉት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተወካይ አምባሳደር ሒሩት ዘመነ ናቸው።
የ2063 አጀንዳን ራዕይ ለማሳካትና የበለፀገች አህጉርን ለመፍጠር አህጉራዊ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ቀልጣፋ ስራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብስባ እየተካሄደ ያለው በየካቲት 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተደረገው 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት ነው።