የፋይዳ መታወቂያ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አበርክቶው የጎላ ነው - አቶ ጌቱ ወዬሳ - ኢዜአ አማርኛ
የፋይዳ መታወቂያ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አበርክቶው የጎላ ነው - አቶ ጌቱ ወዬሳ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 8 /2017(ኢዜአ)፦የፋይዳ መታወቂያ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አበርክቶው የጎላ መሆኑን የሐረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለፁ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ከሐረሪ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር በፋይዳ መታወቂያ ዙሪያ መክሯል።
የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት በብልፀግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ እንደገለፁት ፋይዳ ዜጎች ወጥ ማንነት እንዲኖራቸው በማስቻል የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።
ከዜጎች የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና ሙስናን በመከላከል የዜጎችን እርካታ ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል።
በተለይ የማጭበርበር ወንጀሎችን በማስቀረት የፋይናንስ ዘርፍ ደህንነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።
የፋይዳ መታወቂያ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዙ ግቦችን በማሳካት አበርክቶው የጎላ መሆኑንም ነው የገለፁት።
በቀጣይም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አገልግሎት ከፋይዳ መታወቂያ ጋር ለማስተሳሰር እንደሚሰራ አክለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ምክትል ሀላፊ አቶ ኦላና አበበ በበኩላቸው ፋይዳ መታወቂያ የአገሪቱን ህዝብ ትክክለኛ መረጃ ለይቶ ለማወቅ መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያግዝ እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዜጎች አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያመቻች ስለመሆኑ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።