ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች ነው - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች ነው - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የጀመረችው ሪፎርም በዓለም አቀፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መመዘኛ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትገኝ ማስቻሉን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሚኒስትሮች፣ የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች በተገኙበት እየተገመገመ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የለውጡ መንግስት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ጨምሮ በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ተግብሯል።
በዚህም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተከታታይ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡን አንስተዋል።
የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ በርካታ ውጤቶችን እያስገኘ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምና ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በመተግበር ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል።
አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህ ስራዎች ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መመዘኛ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አስችለዋል ነው ያሉት።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በበኩላቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን አስደናቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
በመድረኩ ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸምን በመገምገም በቀጣይ ሦስት ወራት በትኩረት የሚሠሩ ተግባራት ላይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ጠቁመዋል።