የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢኒሼቲቮች ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው- አምባሳደር ፍስሃ ሻውል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢኒሼቲቮች ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው- አምባሳደር ፍስሃ ሻውል

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ):- መንግስት የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢኒሼቲቮች ተቋማዊ መዋቅር እንዲኖራቸው ለማድረግ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻውል ገለጹ።
ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ ከኢስት አፍሪካ የማዕድን ኩባንያ እና ሙገር ሲሚንቶ ኩባንያ የተወጣጣ የከፍተኛ አመራር ልዑካን ቡድን ለጉብኝት ህንድ ኒው ዴልሂ ይገኛል።
የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት አላማ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ኢኒሼቲቮች ልምድ ለመለዋወጥ እና የእውቀት ሽግግር ለማድረግ ነው።
ልዑኩ በቆይታው በህንድ ያለው የኢንዱስትሪ አሰራሮችን እንደሚጎበኝ በኒው ዴልሂ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማት እና የአረንጓዴ ኢነርጂ ትራንስፎርሜሽን ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጿል።
በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል ከልዑኩ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ከካርቦን ነጻ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት የያዘቻቸውን ግቦች አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢኒሼቲቮች ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።
የከፍተኛ ልዑካን ቡድኑ ጉብኝት እ.አ.አ በ2019 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ይፋ የሆነው “Leadership Group for Industry Transition” የተሰኘው የመንግስት እና የግል አጋርነት ኢኒሼቲቭ አካል ነው።
ኢኒሼቲቩ በህንድ እና ስዊድን መንግስታት የጋራ ሊቀመንበርነት የሚመራ ሲሆን የኢንዱስትሪ ሽግግራቸው ዘላቂነትን የሚከተል ማዕቀፍ ያላቸው አባል ሀገራት የያዘ ነው።
ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በኢኒሼቲቩ አባል የሆኑ የአፍሪካ ሀገራት መሆናቸውን በኒው ዴልሂ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።