የመንግሥት አገልግሎትን የሚያዘምኑና የሚያቀላጥፉ የዲጂታል ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥት አገልግሎትን የሚያዘምኑና የሚያቀላጥፉ የዲጂታል ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 8/2017(ኢዜአ)፦የመንግሥት አገልግሎትን የሚያዘምኑና የሚያቀላጥፉ የዲጂታል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም በተገመገመበት መድረክ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የለውጡ መንግስት የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታን ጨምሮ በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ተግብሯል ብለዋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን ጠቅሰው፥ የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና የዲጅታል ክህሎትና ልህቀትን በመፍጠር ለአካታች ልማት ጉልህ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ልማት ያመጣችው ለውጥ በዓለም አቀፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መመዘኛ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል ነው ያሉት።
ሀገራዊ የመረጃ ቋት በማዘጋጀት የተሻለ የመረጃ ልውውጥ ለመፍጠር የተጀመሩ ተግባራትን የማፋጠን ሥራ ይከናወናል ብለዋል።
መንግሥት ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ለዲጂታላይዜሽን ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው፥ አገልግሎትን ቀልጣፋ የማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አንስተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሃፅዮን በበኩላቸው፥ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ፣የኤክስፖርትና የውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲሁም የመንግስት ገቢን ከማሳደግ አንፃር ትላልቅ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መንግሥት በወሰዳቸው እርምጃዎች የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ረገድ አበረታች ውጤት መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ዲጂታላይዜሽንን በሁሉም ዘርፎች እውን የማድረግ ሥራዎች ውጤታማና ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ናቸው ብለዋል።