ኢትዮጵያ አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመረጠች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመረጠች

አዲስ አበባ ፤ሚያዝያ 9/2017 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ እንደምታስተናግድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥የሀኖይ ጉባኤ አነስተኛ ቢሆኑም በሚገባ የተቀናጁ የፒ4ጂ ፕሮጀክቶች ትርጉም ያለው ውጤት እንደሚያስገኙ እና ለማሳደግም ትልቅ አቅም ያላቸው መሆናቸውን ማሳየቱን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በ2027 የሚካሄደውን አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ ለማዘጋጀት ችቦውን በመረከቧ ኩራት ይሰማታል ብለዋል።
ይኽን እድል በፅናት እና በቁርጠኝነት በመያዝ የቬይትናም፣ ኮሎምቢያ፣ ዴንማርክ እና የኮሪያ ሪፐብሊክን የታየውን ስኬታማ የዝግጅት ውርስ ጨምረን እናስቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል።
ጉባኤው ትብብር፣ ፈጠራ፣ አካታችነት እና ተግባር በተሰኙት የፒ4ጂ አስኳል መርሆዎች እየተመራ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ 2027 ጉባኤ በአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ልማት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና ብሎም ወጣቶችን እና ሴቶችን ማብቃትን የአረንጓዴ ሽግግር ወሳኝ አስፈፃሚ የማድረግ አስፈላጊነትን ትኩረት ሰጥቶ ይዘጋጃልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።